Search

የዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን የሳበው የ5 ዓመቱ የቱሪዝም ልማት ስኬት

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 48

ላለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከናወኑት ግዙፍ የሪፎርም እና የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ አዲስ ምዕራፍ ላይ አስቀምጠዋታል።

አዲስ አበባ ገጽታዋን የሚቀይሩ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኚዎቿ ደግሞ ማራኪ እና ሳቢ መዳረሻ መሆን ችላለች።

ይህ የአምስት ዓመት የሥራ ስኬት ከተማዋን የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ መነቃቂያ ማዕከል በማድረግ የዓለምን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ስቧል።

ከተማዋ በቱሪዝም ዘርፍ ያከናወነቻቸው የኮሪደር ልማት፣ የፓርኮች ግንባታ እና የቅርስ ጥበቃ ሥራዎች ውጤት በተግባር መታየት ጀምረዋል።

አዲስ አበባ ላይ ከተከናወኑት የኮሪደር እና የፓርክ ልማቶች በተጨማሪ በገበታ ፕሮጀክቶች በወንጭ፣ በጎርጎራ፣ በኮይሻ እና በሀላላ ኬላ የተገነቡት የቱሪስት መዳረሻዎችም የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድገውታል።

ለዚህም ማረጋገጫው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው እና ምስክርነታቸውን መስጠታቸው ነው።

ጋናዊው ዩቲዩበር እና ፓንአፍሪካኒስት ዎዴ ማያ፣ አሜሪካዊው አይሾውስፒድ፣ ታዋቂው የማኅበራዊ ሚዲያ የዜና አቅራቢ ዲላን ፔጅ፣ ሌሎች የአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና ታዋቂ ስፖርተኞች ሀገራችንን ከጎበኙት መካከል ናቸው።

እነዚህ ታዋቂ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሳባቸው ባለፉት አምስት ዓመታት በመደመር ትውልድ እሳቤ በቱሪዝም መሠረተ ልማት ላይ የተሠሩት ሥራዎች ውጤት ነው።

አዲስ አበባ ከአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷ ባሻገር አሁን ላይ እንደ ኒውዮርክ እና ጄኔቫ ካሉ የዓለም ትልልቅ የዲፕሎማሲ ከተሞች እኩል ለዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ቀዳሚ ምርጫ እየሆነች ነው።

በቅርቡ ያስተናገደችው የአፍሪካ ማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ 30 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ እና በአጠቃላይ 400 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያላቸውን ታላላቅ የዲጂታል ዓለሙ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በአንድ ላይ ሰብስቧል።

እነዚህ መድረኮች አዲስ አበባን የውይይት ማዕከል ብቻ ሳትሆን፣ የዓለም የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከሚወሰንባቸው ግንባር ቀደም ከተሞች ተርታ አሰልፈዋታል።

በሃና ምንዳሁን