አዝቴካ ስታዲየም በታሪኩ 20ኛውን፤ በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ደግሞ ከ104 ጨዋታዎች የመጀመሪያውን ሊያስተናግድ ሰዓታት ቀርተዋል።
በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ስታዲየም ይህን ያክል ጨዋታ አስተናግዶ አለማወቁም ልብ ይሏል።
የሁጎ ብሩስ ደቡብ አፍሪካ በዓለም ዋንጫ አራተኛ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።
ደቡብ አፍሪካ ራሷ ካስተናገደችው ውድድር 16 ዓመታት በኋላ ነው ወደ ዓለም ዋንጫ የተመለሰችው።
በማጣሪያው ናይጄሪያ የምትገኝበትን ምድብ በቀዳሚነት አጠናቅቃ ለዓለም ዋንጫ የተገኘችው ደቡብ አፍሪካ ከምድብ ተሻግሮ ለማያውቀው የተሳትፎ ታሪኳ በአሜሪካ ምድር አዲስ ተስፋ ሰንቃለች።
በዓለም ዋንጫው ደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅ ሀገርን ስትገጥም ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ በማጣሪያው በአንድ ጨዋታ ብቻ ተሸንፋ ነው ለዓለም ዋንጫ የበቃችው።
ኦስዊን አፖሊስን የያዘው የአጥቂ ክፍል በሜክሲኮ ሲቲው ጨዋታ ቀላል ፈተና እንደማይሆን ይጠበቃል።
ይህ ተጫዋች በማጣሪያው በስድስት ግቦች ላይ ተሳትፎ ነበረው ሲሆን፤ ሁለት አስቆጥሯል አራት ኳሶችን አመቻችቷል።
የማሜሎዲ ሰንዳውንሱ ግብ ጠባቂ ሮንዌን ዊሊያምስም ሌላኛው የትኩረት ማዕከል ነው።
በመድረኩ ለ18ኛ ጊዜ የሚሳተፈው የሜከሰሲኮ ብሔራዊ ቡድን በፉልሀሙ አንጋፋ አጥቂ ራውል ሄሚኔዝ እና የሎኮሞቲቭ ሞስኮው ሴዛር ሞንቴዝ የመሰሉ ተጫዋቾች ላይ ተስፋውን ጥሏል።
የሀቪየር አጉዌር ቡድን ሜክሲኮ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከተሸነፉ ሰባት ጨዋታዎች የተቆጠሩ ሲሆን፤ በአምስቱ አሸንፈዋል በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ዛሬስ? የሁጎ ብሩስ 'ባፋና ባፋና' ከ ከሀቪየር አጉዌር 'ትሪኮለር' የሚያደርጉት ሁለተኛ የእርስ በእርስ ጨዋታ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
ከጥንታዊ የስፍራው ስልጣኔ ስያሜውን የተዋሰው አዝቴካ ስታዲየም፤ እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሌላ የዓለም ዋንጫ ታሪክ ሊያስመዘግብ ምሽት 4:00 ሰዓትን ይጠብቃል።
ጥበቃው እያበቃ ነው። ዓመታት ነጉደው፣ ወራት ተጉዘው፣ ሳምንታት አልቀው፣ ቀናት ተሸኝተው ሰዓታት ብቻ ቀርተዋል።
ወድቆ መነሳት፣ ጣፋጭ ድል፣ መራር ሽንፈት፣ ህብረ-ቀለማዊ ትዕይንት፤ እነዚህን ሁሉ ትዝታዎች ይዞ ባለ 48 ሀገራቱ የዓለም ዋንጫ ተመልሷል።
በእድሪስ አህመድ