Search

የኢትዮጵያ አዲሱ የዲጂታል አብዮት

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 56

ዓለማችን በቴክኖሎጂ ማዕበል እየገሰገሰች፣ የሰው ልጅ የእውቀት እና የፈጠራ አድማስ በየሰከንዱ እየሰፋ እና ፍጥነቱ እና ተለዋዋጭነቱ እያደገ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ የራሷን አዲስ የዲጂታል አብዮት ትርክት በደማቁ እየጻፈች ትገኛለች።

የዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ዋነኛ ማሳያ ደግሞ፣ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕጣ ፈንታ ለመቀየር እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የተጠነሰሰው "5 ሚሊዮን ኢትዮጵያ ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ ያስመዘገበው አንፀባራቂ ስኬት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ዛሬ እንዳበሰሩት፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት ተችሏል።

ሐምሌ 16 ቀን 2016 . ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፣ በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ በመረጃ ትንተና፣ በአንድሮይድ ሶፍትዌር ልማት እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ ትምህርቶች 5 ሚሊዮን 5 ሺህ 146 ሠልጣኞች ተመዝግበው 3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ስልጠናውን አጠናቀዋል።

ይህ ድል የኢትዮጵያ ወጣቶች ወሰን የሌለው አቅም እና የሕዝባችን የልማት ቁርጠኝነት ሕያው ማረጋገጫ ነው።

ይህ ስኬት በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን፣ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ከተሰኘው ሰፊ ሀገራዊ ራዕይ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን እና የብሔራዊ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን ተቋማዊ አቅም በማሳደግ የሀገራችንን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጡ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ለዘርፉ ሽግግር ወሳኝ የሆነውን የሰው ኃይል ለማልማት፣ በመደበኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሠሩ ሥራዎች በተጨማሪ ይህ "የኢትዮ ኮደርስ" ፕሮግራም መተግበሩ፣ ሀገራችን ከባህላዊ ኢኮኖሚ ወደ እውቀት-መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር አስተማማኝ መደላድል የፈጠረ ትልቅ ስኬት ነው።

የፋይዳ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት፣ ቴሌብር እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የዳበሩት "መላ" እና "ቀና" አፕሊኬሽኖች፣ ይህ የሠለጠነ የሰው ኃይል የሚያንቀሳቅሳቸው የዲጂታል አብዮታችን ምሰሶዎች ናቸው።

የዲጂታል ክህሎት በአንድ ሀገር መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ላይ ያለውን ፋይዳ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ሕንድ ወጣቶቿን በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በስፋት በማሠልጠን፣ የዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መዳረሻ እና የአገልግሎት አቅርቦት ማዕከል በመሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ከድህነት አውጥታለች።

በሌላ በኩል ኢስቶኒያ ከሶቭየት ኅብረት መፍረስ በኋላ፣ ለዜጎቿ ገና በልጅነታቸው ኮዲንግን በማስተማር "-ኢስቶኒያ" (e-Estonia) በመባል የምትታወቅ፣ አብዛኛው የመንግሥት አገልግሎት በቴክኖሎጂ የሚመራባት የአውሮፓ ዘመናዊ ዲጂታል ማኅበረሰብ ለመገንባት በቅታለች።

ደቡብ ኮሪያ ደግሞ በዲጂታል ዕውቀት እና በኢንተርኔት መሠረተ-ልማት ላይ ባደረገችው ግዙፍ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂን የኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት በማድረግ ታላላቅ የበለጸጉ ሀገራት ተርታ ተቀላቅላለች።

እነዚህ ተሞክሮዎች የሚያሳዩት የኢትዮጵያ የኮደርስ ፕሮግራም ሀገራችንን ከዓለም የቴክኖሎጂ ፉክክር ተርታ ለማሰለፍ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንዳሰመሩበት፣ በዲጂታሉ ዓለም በልኩ ለመዘጋጀት የጀመርነው ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ የጉዟችን ማብቂያ ሳይሆን ብሔራዊ ርዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት መነሻ ነው።

እስከ ነሐሴ 2018 . ድረስ የሠልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ አዲስ ግብ ተሰንቋል።

ይህን ለማሳካት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚህ ብሔራዊ ተልዕኮ አካል ሊሆን ይገባዋል። በተለይም ለወጣት ተማሪዎቻችን መጭው የክረምት ወቅት ትልቅ ዕድል ነው።

ወጣቶች ጊዜያቸውን በዋዛ ከማሳለፍ ተቆጥበው፣ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነውን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለውን የምስክር ወረቀት የሚያስገኘውን ይህን ሥልጠና በመውሰድ፣ የዓለም አቀፍ የዲጂታል መሪዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል አብዮት ከወረቀት ወደ ተግባር፣ ከተስፋ ወደ ተጨባጭ እውነት ተሸጋግሯል። ይህ ፕሮግራም ትውልዱ የዲጂታል መሣሪያዎችን ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ እና የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆን መንገዱን በሰፊው ጠርጓል።

ልክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ "የምትገነቡት ነገ የሚጀምረው ዛሬ ነው!" ይህ የዛሬው ዕውቀት እና ክህሎት፣ የነገዋ የበለጸገች እና ታላቅ ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ነው።

የዲጂታል ዘመን መሪ ለመሆን ዛሬውኑ ይቀላቀሉ - www.ethiocoders.et

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ