Search

ከኢኮኖሚ ሞተርነት እስከ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደምትነት

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 42

ሀገራችን ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በአፍሪካ ብሎም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ዘንድ ተፅዕኖዋ ከፍ እያለ መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ በቀጣናው የጸጥታና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ያላት ድርሻ እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ያላት የጎላ ሚና የሚመነጨው ካላት ታሪካዊ ዳራ ባሻገር በምታሳካው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖም ጭምር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ግዝፈት ከሀገር በቀል ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት፣ ከምግብ ሉዓላዊነት እና ከዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚመነጭ ቢሆንም በሌላ መልኩ ሰፊ የሕዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ የትምህርት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት የምታራምደው ስትራቴጂካዊ የለውጥ መንገዶችና ስኬቶች ናቸው፡፡

የአፍሪካ ቀንድ በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጡ እጅግ ስትራቴጂካዊ በተመሳሳይ ደግሞ በተለዋዋጭ የፖለቲካ ውጥረቶችና አለመረጋጋቶች የሚታወቅ ቀጣና ነው።

በቀጣናውም የኢትዮጵያ ጠንካራ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አቅም መገንባት ለሀገር ውስጥ እድገት ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ቀጣና ሰላም፣ መረጋጋት እና የጋራ ብልጽግና ዋስትና መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው።

የኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም በቀጣናው ውስጥ እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ ሞተር ሆኖም ያገለግላል።

በመሠረተ ልማት ትስስር ኢትዮጵያ የምታመነጨውን ታዳሽ ኃይል ጎረቤት ለሆኑ ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ሱዳን ሀገራት በማቅረብ የቀጣናውን የኃይል እጥረት ከመቅረፍ ባለፈ የኢኮኖሚ ትስስሩን እያጠናከረች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ሰፊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍላጎት ጎረቤት የሆኑ ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የወደብ መሠረተ ልማታቸውን እንዲያሳድጉና ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኙ ዕድል መፍጠር ችሏል።

130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የገዥነት አቅሟና የፖለቲካል ኢኮኖሚዋ ሲጠነክር ለቀጣናው ሀገራት ምርቶች ሰፊና አስተማማኝ ገበያ የመፍጠር እድል ከፍተኛ እንደሆነም የአደባባይ ሀቅ ነው።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና ፀጥታ እንደ ጠንካራ ግንብ ሆና ከማገልገል ባሻገር ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት በቀጣናዊ ቀውሶች ተሰድደው ወደ ግዛቷ የገቡትን ዜጎች አቅፋ የምታስተናግድ ሀገር ናት፡፡

ሀገራችን የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆንም የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ በቀጣናው የሚነሱ ግጭቶችን በውይይትና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን የመደራደርና የማስታረቅ አቅም አመላካች ነው፡፡

የአፍሪካ ቀንድ የዓለም ኃያላን ሀገራት ፍላጎትና ሽኩቻ የሚያርፍበት ቀጣና እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚዋ ጠንካራ እየሆነች በመምጣቷ ባዕዳን ኃይሎች በቀጣናዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የራሳቸውን አጀንዳ ብቻ እንዳይጭኑ የመከላከል አቅም ፈጥራለች፡፡

ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው መርህ እውን ሊሆን የሚችለው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ሲጠነክሩ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ባሕር በር የሌላት ሀገር ብትሆንም የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ሰላምና ደኅንነት ላይ ቀጥተኛ ሚና ካላቸው ሀገራት ተርታ ትመደባለች፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ከቀጣናው አልፎ በመላው አፍሪካ ትልቅ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የኢትዮጵያ ጥንካሬ የአሕጉሪቱ ዋስትናም ጭምር ነው፡፡

በንፍታሌም እንግዳወርቅ