ኢትዮጵያ በተለይም መዲናዋ አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት።
ይሁንና ይህን ሰፊ ዕድል ተጠቅማ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ በአህጉሪቱ ቀዳሚ ስፍራ ለመያዝ የነበራትን አቅም ለረጅም ጊዜ በበቂ ሁኔታ ሳትጠቀምበት ቆይታለች።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ይህን ታሪክ የሚቀይር መጠነ-ሰፊ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል።
የተጨባጭ ስኬቶች ማሳያ እና የማስተናገድ ብቃት
ሀገራችን በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ኮንፈረንሶችን በብቃት ማስተናገዷ የዘርፉ ዕድገት ምን ያህል እየተፋጠነ መሆኑን ያሳያል።
በተለይም ከ25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበትን ሁለተኛውን የአፍሪካ የዓለም አየር ንብረት ጉባኤ በታላቅ ስኬት ማጠናቀቋ፣ የኢትዮጵያን ግዙፍ እና አስተማማኝ የማስተናገድ ብቃት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተግባር ያሳየ ትልቅ ስኬት ነው።
ለዚህም ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ የኮንፈረንስ ማዕከላት ናቸው።
የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት እና የኢሲኤ (UNECA) ታሪካዊ አዳራሾች ከተማዋን ለኮንፈረንስ ተመራጭ እያደረጓት ነው።
በተለይም ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባው አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ማንኛውንም ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በተሟላ ሁኔታ የሚያስተናግድ ነው፡፡
ግዙፉ ማዕከል አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እና የንግድ ትርኢቶች ማዕከል ያደርጋታል።
በተጨማሪም የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋን ለዓለም አቀፍ እንግዶች ይበልጥ ሳቢ ምቹ እና ደኅንነቷ የተጠበቀ እንድትሆን በማድረግ ለቱሪዝሙ ትልቅ አቅም ፈጥረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የደንዲ ኢኮ ሎጂን በመረቁበት ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ እስከ 80 ሺህ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ለመፍጠር ዒላማ አድርጋ እየሠራች ትገኛለች።
ይህ ራዕይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በገበታ ፕሮጀክቶች ከተገነቡት ዓለም አቀፍ ሪዞርቶች፣ እንዲሁም ከመላው ዓለም ጋር በቀጥታ ከሚያገናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በመዲናዋ ካሉ ባለኮከብ ሆቴሎች እና ፓርኮች ጋር ተዳምሮ አቅሙን እጅግ አሳድጎታል።
የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት
የኮንፈረንስ ቱሪዝም ወቅትን የማይጠብቅ በመሆኑ ለሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ ግብዓት ነው።
ለሆቴሎች፣ ለአየር መንገድ፣ ለቱሪዝም አስጎብኚዎች፣ እንዲሁም በሥራ ፈጠራው ዘርፍ ሰፊ ዕድል በመፍጠር የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ከስብሰባ ጎን ለጎን እንግዶች የእንጦጦ፣ ወዳጅነት እና ሸገር ፓርኮችን መጎብኘታቸው የከተማ ቱሪዝምን ይበልጥ እያነቃቃው ነው።
ወደ ፊት፦ ኮፕ 32 (COP32)
በዓመት ከ150 ኮንፈረንሶችን እና በአንድ ጊዜ ከ25 ሺህ ሰዎች በላይ የተሳተፉበትን ጉባኤ በስኬት የማስተናገድ ብቃት ኢትዮጵያ ያላትን የላቀ ዝግጁነት ለዓለም በተግባር አሳይተዋል።
ይህ አቅም ደግሞ 32ኛውን የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP32) ለማስተናገድ የአፍሪካ ኅብረትን ሙሉ ድጋፍ አግኝታ በእጩነት እንድትመረጥ ማስቻሉ ነው።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ ሳይንቲስቶች እና የፖሊሲ አውጭዎች የሚገናኙባት የኢንቨስትመንት መዲና በማድረግ፣ የሀገርን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ የሚያግዝ ትልቅ የኢኮኖሚ ሞተር ነው፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ