ኢትዮጵያ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ የሚያሳልጥ አዲስ ታሪክ ጽፋለች።
ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት በማስታጠቅ ለነገው ዓለም ዝግጁ ለማድረግ የተወጠነው "የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ የተቀመጠለትን ግብ ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ በማሳካት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
ይህ ስኬት የቁጥር ዕድገት ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በእጅጉ የሚያፋጥን ታላቅ እመርታ ነው።
ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ጋር በመተባበር የተጀመረው ይህ ግዙፍ ሀገራዊ ንቅናቄ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂን መነሻ ያደረገ እና ወደ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" የምናደርገውን ጉዞ የሚያቃና ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች እንደገለጹት፣ እውነተኛው የሀገር ሀብት የሰለጠነ የሰው ኃይል በመሆኑ፤ ወጣቶች የነገውን ዓለም በዕውቀት እንዲመሩ የክህሎትን ቁልፍ ማግኘት አለባቸው።
5 ሚሊዮን ኮደሮችን የማፍራት ግብ መሳካቱ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ወደ ውጤት የሚቀይር ነው።
ይህ ፕሮግራም ወጣቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሊያደርጓቸው በሚችሉ እንደ ድረ-ገፅ ግንባታ፣ የሞባይል መተግበሪያዎች፣ የዳታ ሳይንስ እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ባሉ ዘመናዊ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል።
ስኬቱ የሀገር ውስጥ ፍላጎቶችን በሀገር በቀል አቅም ለመመለስ፣ አገልግሎቶችን ለማዘመን እና ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የርቀት ሥራዎችን እየሠሩ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገቡ ትልቅ በር ይከፍታል።
ይህን ትልቅ ቁጥር ማሳካት ቀላል ባይሆንም በመንግሥት ቁርጠኝነት፣ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና በወጣቶች ታታሪነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ዲጂታል አብዮት ማሳካት ተችሏል።
የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ስኬት የጉዟችን ማጠቃለያ ሳይሆን ሀገራችንን ወደ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" የረጅም ጊዜ ራዕይ የሚያሻግረን ጉዞ መጀመሪያ ነው።
እነዚህ ወጣቶች የኢትዮጵያን ዲጂታል ምሕዳር የሚቀይሩ እና ሀገራችን በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ መድረክ ከፍ እንድትል የሚያደርጉ የነገ መሪዎች ናቸው።
የዚህ ኢኒሼቲቭ ስኬት የኢትዮጵያ ዲጂታል ሕዳሴ በተግባር እየታየ ስለመሆኑ እና “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ከግብ እንደሚደርስ ትልቅ ማረጋገጫ ነው።
በሔዋን ጌታቸው