Search

የጉምሩክ ማሻሻያ አዋጅ ፀደቀ

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 424

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ24ኛ መደበኛ ስብሰባው የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፅድቋል።

‎በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

‎

ረቂቅ አዋጁ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ሰብሳቢው ገልጸዋል።

‎

ረቂቅ አዋጁ በዘርፉ ሀገራችን ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የሚያስችል ሲሆን፣ በጉምሩክ አሠራር ውስጥም ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።

‎

‎በተጨማሪም፣ ረቂቅ አዋጁ በሀገራችን እያደገ የመጣውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደግፍ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑን የኮሚቴው ሰብሳቢ አመላክተዋል።

‎

‎ረቂቅ አዋጁ በነባሩ አዋጅ ውስጥ የተደነገጉ ገደቦችን በተግባር ላይ ሲውሉ ይስተዋሉ የነበሩ የአተገባበር ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችሉ ዘንድ አስፈላጊ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑንም አንስተዋል።

‎

‎አስመጪዎች በቀረጥ እና ታክስ አወሳሰን ላይ ያላቸውን አቤቱታ በማቅረብ ሂደት ያጋጥሟቸው የነበሩ የአሠራር መሰናክሎችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎

‎የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ወቅት የተከናወነው ሥራ አስፈላጊውን የሕግ ምርመራ እና ግምገማ ሂደት የተከተለ መሆኑን እና አዋጁም በተገቢው ሁኔታ ታይቶ እና ተገምግሞ የቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

‎

‎በኮንትሮባንድ ጭነት ምክንያት ተሽከርካሪ እንዲወረስ የሚያስችል ድንጋጌ ቢኖርም፣ ባለቤቱ በድርጊቱ ተሳታፊ ባልሆነበት ሁኔታ ንብረቱ ሊወረስ እንደማይገባም አንሥተዋል።

‎

‎ባለቤቱ ተሽከርካሪውን አሽከርካሪ እንዲጠቀምበት በውል ሲያስረክብ፣ ታማኝና ለሕግ ተገዥ የሆነ ሹፌር መቅጠር እንዲሁም ለሚደርስ ጉዳት ወይም ሕገ-ወጥ ድርጊት ተገቢ ዋስትና መውሰድ እንዳለበት ተጠቁሟል።

‎

‎ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን፣ አዋጅ ቁጥር 1425/2018 አድርጎ በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: