የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢቢሲ የሚዲያ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በለጠ እሱባለው፤ የኢቢሲ ዶትስትሪም መቋቋም በዲጂታል ሚዲያው ላይ ትልቅ ስራ ለመስራት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
ዲጂታል ሚዲያን እንደ ትርፍ ማየት የነበረው አሠራር ወደ ኋላ አስቀርቶን ነበር ያሉት አቶ በለጠ፤ የኢቢሲ ዶትስትሪም አዲስ አደረጃጅት ይህን አመለካከት ለመቀየር አስችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም አቢሲ በሁሉም አማራጮች በቀላሉ ሰዎች ጋር ለመድረስ የሚያስችለውን የሞባይል መተግበሪያ እና ድረ ገፅ በመስራት ተደራሽነቱን ይበልጥ ማሳደጉን ገልጸዋል።
ኢቢሲ በየጊዜዉ ተቀያያሪ ከሆነዉ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ በመጓዝ እንዲሁም አዲስ የይዘት ማሻሻያዎችን በማድረግ ከዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር አብሮ በመጓዝ ተደራሽነቱን ከፍ ማድረጉንም አንስተዋል።
ኢቢሲ ከዚህ በፊት ይከተለው የነበረዉ አሰራር ወረቀትን መሰረት ያደረገ ነበር ያሉት አቶ በለጠ፤ ይህም ጊዜ የሚወስድ፣ ወጪ ጠያቂ፣ የዉስጥ ለዉስጥ አሰራርን የሚያንጓትት መሆኑ በርካታ ስራዎች እንዳይሰሩ ተግዳሮት ሆኖ እንደነበር ተናግረዋል።
ይህን ችግር በማየት አሰራሩን መሉ በሙሉ በመቀየር ከወረቀት ነፃ የሆኑ የተለያዩ መተግበሪያዎች በማበልፀግ ስራዎችን በአጭር ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ በመሆነ መንገድ ለመስራት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።
ከዲጂታል ሚዲያዉ ጋር አብሮ ለመጓዝ ኢቢሲ ዶትስትሪም ዉስጥ ትልቅ ተቋም እና አደረጃጀት በመፍጠር በዲጂታል ሚዲያ ላይ ትልቅ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።
በቢታንያ ሲሳይ
#EBC #ebcdotstream #Digital_EBC #DigitalEthiopia #EBCApp