Search

የኢቢሲ የዲጂታል ትግበራ ለሌሎች ተቋማት ተሞክሮ የሚሆን ነው - ቢልለኔ ስዩም

Aug 13, 2025

ኢቢሲ የጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ ለሌሎች ተቋማት ተሞክሮ የሚሆን ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ "ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የዲጂታል ሚዲያው ሚና ምንድን ነው" በሚል በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ አስተያየት የሰጡት ቢልለኔ ስዩም፤ ኢቢሲ በዲጂታል ኢትዮጵያ ማንኛውም ተቋም ወደ ኋላ መቅረት የለበትም የሚለውን መርህ እንደ ሚዲያ ተቋም አንድ እርምጃ ወስዶ በተግባር ማሳየቱ ያስመሰግነዋል ብለዋል።

ኢቢሲ ባበለፀገው መተግበሪያ የቋንቋ፣ የሬድዮ እና የተለያዩ ዜናዎች በአንድ ላይ እጃችን ላይ ባለ ስልክ እንድናይ ማስቻሉ ትልቅ ነገር ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ኢቢሲ የጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ ለሌሎች ተቋም ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነው ያሉት ቢልለኔ ስዩም፤ ሌሎች ተቋማትም ይህንኑ መነሻ በማድረግ እሴት ጨምረው ተሞክሮውን ሊተገብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ያለንበት ዓለም ተለዋዋጭ ስለሆነ ለማህበረሰቡ ታዓማኒነት ያለው ትክክለኛ መረጃን በቀዳሚነት ከማቅረብ ረገድ እንደዚህ አይነት የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኢቢሲ አሁን ላይ በየኪሳችን መጥቷል ያሉት ቢልለኔ ስዩም፤ ኢቢሲ በላቀ ደረጃ ወደ ህዝቡ መድረስ መቻሉ ብዙ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀዋል።

በሔለን ተስፋዬ

#EBC #ebcdotstream #Digital_EBC #DigitalEthiopia #EBCApp