Search

በአዲስ አበባ አዲሱ የተሽከርካሪ ሠሌዳ መሰጠት ጀመረ

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 112

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘገየ በላይነህ አዲሱ የተሽከርካሪ ሠሌዳ ከዛሬ ጀምሮ መሰጠት መጀመሩን ገለጹ።

አዲሱ ሠሌዳ ሀገራዊ የሆኑ ይዘቶችን ያካተተ መሆኑን እና ኮፒ ወይም ፎርጂዲ የማይሠራበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን አገልግሎቱን ለማዘመን ቁጥጥሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ለዚህም አዲሱን የተሽከርካሪ ሠሌዳ አጠቃላይ ይዘት አተገባበር ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ሥራዎችን ለማዘመን እንዲሁም ኢትዮጵያን የሚገልጹ መለያዎችን የያዘ እና ዓለም አቀፍ መስፈርቱን የተከተለ ነው ብለዋል።

ሠሌዳው የተለያዩ መረጃዎችን የሚይዝ በመሆኑ ለሕግ ማስከበር ሥራ የሚመች፣ ቶሎ የማይበላሽ እና ወጪ ቆጣቢ መሆኑን አብራርተዋል።

አሁን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ያለው አዲስ ለሚገዙ መኪኖች አገልግሎቶች የሚጀመር መሆኑን እና ከዚህ በፊት ሠሌዳ ለሌላቸው አገልግሎቱ በቅርብ እንደሚጀመር ገልጸዋል።

ሠሌዳው ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መሰጠት መጀመሩን እና ተገልጋዮች በተመዘገቡበት ቅደም ተከተል እንደሚወስዱ፤ በክልል ከተሞች ደግሞ በቅርቡ እንደሚጀምር ተገልጿል።

በቢታንያ ሲሳይ