ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ እየሳበ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልሰ አብዲሳ ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን የሥራ እንቅስቃሴ በዛሬው ዕለት ተመልክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በኢኮኖሚ ለማብቃትና የኦሮሞ ሕዝብን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የታለመና የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው ሥራ መጀመራቸውን አመልክተዋል።
በዚህም መሠረት ባለሃብቶቹ በንግድ፣ ሎጂስቲክስ፣ ግብርና እና የግብርና ምርት ማቀነባበር፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ አገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።
በኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶችን ጨምሮ የቻይና፣ የአሜሪካ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን እና የሌሎች ሀገራት ባለሃብቶች መሰማራታቸው ተጠቅሷል፡፡
ይህም ቀጣናው የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ በመሳብ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ማሳያ መሆኑ መገለጹን የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።