የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የዲላ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ክልሉ በ6 ማዕከላት የተደራጀ በመሆኑ የተበታተኑ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል መስጠት አገልግሎቶችን ለማሳለጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ ዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎትን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ጥራትና ቀልጣፋ አገልግሎትን እንዲያገኙ የሚያስችል ኢንሼቲቭ መሆኑን አመልክተዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ መጀመሩ ብልሹ አሠራሮችን በማስቀረት ግልጽነትን ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ታሪክን እየቀየረ ያለ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ቢሮክራሲን የቀነሰ እንዲሁም የዜጎችን ክብር የሚመጥን እንዲሆን በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ለዲላ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋም ግንባታ ከ413 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ገልጸዋል።
የዲላ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 32 የመንግሥት አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ እንደሚሰጥም ተመላክቷል፡፡
በተመስገን ተስፋዬ