የአንድ ከተማ ነዋሪዎችን መረጃ በዘመናዊ መንገድ ማደራጀት ሰነድ ከማስቀመጥ ባለፈ የዕለት ተዕለት አገልግሎትን ለማቅለልና ለሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ሰነዶችን በዘመናዊና በዲጂታል መንገድ ለማደራጀት እያከናወነ ያለውን ሥራ በአካል ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ወቅት ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታላይዜሽን ጉዞ በተግባር መሬት እየረገጠ እንተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ አማካኝነት የተመዘገቡ ስኬቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
ኤጀንሲ የጀመረው የሰነድ አስተዳደር ሥርዓት ሀገሪቱ ለያዘችው የዲጂታል 2030 ራዕይ መሳካት ትልቅ ስንቅ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ይህም ሥራ በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ሊሰፋና ሊቀመር የሚገባ መሆኑን አንስተው፣ ዜጎች ባሉበት ሆነው በቀላሉ መረጃዎችንና አገልግሎቶችን በኦንላይን ማግኘት የሚችሉበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ትልቅ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሴ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በየጊዜው የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ከ50 ሚሊዮን በላይ ዲጂታይዝ ከሚደረጉ መረጃዎች ውስጥ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ መረጃዎች ዲጂታይዝ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በወይንሸት ደጀኔ