በሐረሪ ክልል ሐረር ከተማ በ96 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባው ሪጅናል ላብራቶሪ በዛሬው እለት ተመርቋል።
የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ላብራቶሪውን መርቀው ከፍተዋል።
ማዕከሉ ለምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሕክምና አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የላብራቶሪው መመረቅ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ስራን በማዘመን የዜጎች የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።
ላብራቶሪው በክልሉ እና በአጎራባች ክልሎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት መነሻ በማድረግ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።
የላብራቶሪው መገንባት በክልሉ የተጀመረውን የጤና ኮሪደር ልማት በማላቅ፣ በአካባቢው ከሚገኙ የግል እና የመንግስት የጤና ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ለመተግበር እንደሚያግዝም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ ባለፉት 7 ዓመታት የጤና ፖሊሲን ከማሻሻል ጀምሮ በሽታን መከላከል እና አክሞ ማዳንን መሰረት ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ለውጦች በጤናው ዘርፍ ላይ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
የጤና የመሰረተ ልማቶችን በማስፋፋትና ቁሳቁሶችን በማሟላት በከተማ እና በገጠር የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት 7 ዓመታት ውስጥ ዓለም አቀፍ መመዘኛን የሚያሟሉ 28 ላብራቶሪዎችን መገንባት እንደተቻለ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
በቴዎድሮስ ታደሰ