Search

የ5ቱ ዓመታት ገጾች፦ ከትዝታ ማኅደርነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ሞተርነት የተሸጋገሩት የኢትዮጵያ ቅርሶች

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 70

ኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ታሪክ ያላት፣ በሰው ልጅ መገኛነቷ የምትታወቅ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ (UNESCO) የተመዘገቡ በርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት የሆነች ሀገር ናት፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን ታላቅ ታሪካዊና ባህላዊ እምቅ ሀብት በሚገባ ሳትጠቀምበት ረጅም ዘመናትን በትዝታ እና በትረካ ብቻ አሳልፋለች።

ዛሬ ግን ይህ የታሪክ መጋረጃ ተገልጧል። ኢትዮጵያ በአዲሱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና 10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ይህንን መዋቅራዊ ስብራት በመቀየር፣ ቱሪዝምን እና የቅርስ ጥበቃን የሁለንተናዊ ብልጽግናዋ ዋነኛ ምሰሶ አድርጋለች።

ቱሪዝምን የኢኮኖሚ ሞተር ባደረገው በዚህ አዲስ ስትራቴጂ፣ የቆዩ ቅርሶች ታድሰውና ተጠብቀው ወደ ሕያው ብሔራዊ ሀብትነት እየተቀየሩ ይገኛሉ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከተሠሩት ሥራዎች መካከል ለቅርሶች ጥበቃ እና መልሶ ማልማት የተሰጠው ትኩረት እጅግ የጎላ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ታሪካዊ ቅርሶች በዘላቂነት ለመጠበቅ ከሀገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ጠንካራ አጋርነት ፈጥሯል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው "ዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት" ነው።

በዚህም የውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን መዋቅራዊ ደኅንነት ለመጠበቅ እና ከአደጋ ለመታደግ በርካታ አስቸኳይ የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።

የቅብ ሥዕሎች፣ የብራና መጻሕፍት እና የውስጥ መብራት መስመሮች ጥበቃ በልዩ ጥንቃቄ የተከናወነ ሲሆን 100 በላይ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እና ተማሪዎች በቅርስ አስተዳደርና ጥገና ሥልጠና አግኝተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሌላው ትልቅ ትኩረት ያገኘው የጎንደር አብያተ መንግሥታት እና አብያተ ክርስቲያናት ዕድሳት ነው።

የጎንደር ከተማ መለያ የሆኑትን ጥንታዊ አብያተ መንግሥታት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ታሪካዊ ቦታዎችን ዕድሜ ለማራዘም እና ቀድሞ የነበራቸውን ድንቅ የሥነ-ሕንፃ ጥበብ ጠብቀው እንዲቆዩ ከፍተኛ የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።

ይህ ጥረት የአካባቢውን መንፈሳዊ እና ታሪካዊ እሴት ከመጠበቅ ባለፈ፣ ጎንደርን የዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ዋነኛ መዳረሻነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አድርጓታል።

በተመሳሳይ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል በዩኔስኮ የተመዘገበችው ታሪካዊቷ የሐረር ጀጎል ከተማ ሌላዋ የቅርስ ጥበቃ ስኬት ማሳያ ናት።

የከተማዋን ጥንታዊ ግንብ፣ ታሪካዊ መሥጊዶችን እና የነዋሪዋን መለያ የሆኑትን የሐረሪ ባህላዊ ቤቶች (ጌጋር) ልዩ የሥነ-ሕንፃ ጥበብ ሳይለቁ የማደስና የመንከባከብ ሥራዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ዕድሳቱ ሐረር የሰላም፣ የአብሮ መኖር እና የፍቅር ተምሳሌትነቷን ይበልጥ እንድታጎላ ከማድረጉም ባሻገር፣ የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።

የቱሪዝም እና የቅርስ ጥበቃ ሥራ በዋና ከተማችንም ጉልህ አሻራ እያሳረፈ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራ የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየርና መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ለታሪካዊ ሕንጻዎች እና ቅርሶች ጥበቃ የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ ነው።

በተለይም በፒያሳ እና በአራዳ አካባቢዎች የሚገኙ ጥንታዊ ሕንጻዎች ታሪካዊ ይዘታቸውን ሳይለቅቁ እንዲታደሱ እና እንዲጠበቁ መደረጉ አዲስ አበባን ምቹ፣ ጽዱ እና ታሪኳን አጉልታ የምታሳይ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ እንድትሆን አስችሏታል።

በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) የገንዘብ ድጋፍ እና በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥረት ዕድሳቱ የተጠናቀቀው የብሔራዊ ቤተ መንግሥትም የዚሁ የከተማ ቱሪዝም ስኬት ማሳያ ነው።

ቤተ መንግሥቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቶ ሊፈርስ ተቃርቦ ከነበረበት ሁኔታ ድኖ፣ ወደ ሕያው የታሪክ መዝገብነት ተለውጦ ለእይታ ክፍት ሆኗል።

በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሳሽነት የተተገበሩት የገበታ ፕሮጀክቶች ተፈጥሮን እና ታሪክን በአንድ ላይ በማጣመር ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።

በጣና ሐይቅ ሰሜናዊ ዳርቻ የተገነባው የጎርጎራ ፕሮጀክት 17ኛው ክፍለ ዘመን የአፄ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት እና 700 ዓመታት ታሪክ ያላትን የደብረ ሲና ማርያም ቤተክርስቲያንን ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ያካተተ ነው።

የሪዞርቱ ሥነ-ሕንፃ የጎንደር ግንቦችን የታሪክ አሻራ በሚያሳይ የድንጋይ ጥበብ የተገነባ ሲሆን ታሪካዊ ቅርሶቹ ይዘታቸውን ሳይለቁ ታድሰው የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ ከትውልድ ጋር እንዲያስተሳስሩ ተደርጓል።

'ገበታ ለሸገር' ፕሮጀክት ታድሶ ድንቅ ውበቱን የተላበሰው የአፄ ምንልክ የግብር አዳራሽ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ገጽታ ከሚያጎሉ ቅርሶች አንዱ መሆኑ ተገልጿል።

የአባ ጂፋር ቤተመንግሥት ከመፍረስ አደጋ ድኖ በልዩ ውበት መታደሱ የኢትዮጵያ ሌላኛው የታሪክ እና የቱሪዝም ሀብት አድርጎታል።

በተመሳሳይ የወንጪ ኢኮ ሎጅ ሲገነባ በሐይቁ ላይ የሚገኘው ጥንታዊው የወንጪ ቂርቆስ ገዳም ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲታደስ እና የጎብኚዎች መዳረሻ እንዲሆን ተደርጓል።

እነዚህን የተከናወኑ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች ለቀጣዩ ትውልድ በታማኝነት ለማስተላለፍ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ ዲጂታል አርካይቭ ሥርዓት እየተሸጋገረች ትገኛለች።

የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በዩኔስኮ የተመዘገቡ ግዙፍ ሀገራዊ ቅርሶችን እና ታሪካዊ ሰነዶችን በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሰናዳት የሚያስችል ልዩ ሥርዓት እየዘረጋ ይገኛል።

ይህ መዋቅር የኢትዮጵያን ቅርሶች ከማንኛውም የተፈጥሮም ሆነ የሰው ሠራሽ አደጋ ታድጎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ያሰፋዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ታሪካዊ እና ባህላዊ ሀብቶች እያሏት ሳትጠቀምባቸው የኖረችበትን አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ በአዲሱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሪነት ሙሉ በሙሉ እየቀየረችው ትገኛለች።

ዛሬ ላይ የቅርስ ጥበቃ ሥራዎቻችን ታሪክን ከመጠበቅ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ለሀገር ውስጥ ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥሩ እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን እና ዲፕሎማሲን የሚያጠናክሩ እውነተኛ ብሔራዊ ሀብቶቻችን ሆነዋል።

ይህ ስትራቴጂያዊ ሽግግር፣ ኢትዮጵያ የነበራትን እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ ብልጽግና በመቀየር ወደፊት እያደረገችው ላለው የዕድገት ጉዞ ትልቅ ማረጋገጫ ነው።

በለሚ ታደሰ