የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አካሂዷል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመተባባር የአምስት አቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ እና እድሳት፣ ችግኝ ተከላ እና ለ1 ሺህ 700 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አከናውኗል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ ሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋማቱ በክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ በመላው ሀገሪቱ 35 የሚሆኑ የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ እንዲሁም 200 ሺህ የሚሆኑ ችግኞች እንደሚተክል ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሯ ከዕቅድ በላይ ማሳካክቷን አንስተው፤ እስከ ነሐሴ መጨረሻ 8 ቢሊዮን ችግኞች ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደመገኘቱ፣ በአካባቢው የሚተከሉ ችግኞች ትልቅ ሀገራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡ የአቅመ ደካማ ቤቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መረሐ ግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በነስረዲን ሀሚድ