በቱርኬሚስታን አዋዛ ከተማ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት 3ኛው የባሕር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ጉባዔ፤ የባሕር በር ጥያቄያችን ተገቢ መሆኑን ያሳየንበት ነው ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ከባሕር በር በመራቅ እና አማራጭ በማጣት ሀገራቱ የሚገቡበት ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለመቀነስ የተፈረመው የአዋዛ ሰነድ ስምምነት፣ እ.ኤ.አ ከ2024 እስከ 2034 ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ታልሟል፡፡
ስምምነቱ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ፍትሐዊ እና የተሳለጠ ኮሪደር እንዲያገኙ የሚደግፍ መሆኑን ዶ/ር ፈቲህ ማህዲ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል።
በጉባዔው ላይም ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላቸው ሁሉም ሀገራት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ከባሕር ላይ መሸጋገሪያ ባለፈ አስተማማኝ እና እርግጠኛ የሆነ አማራጭ ሊያገኙ ይገባል የሚለው አቋሟን ማንፀባረቋን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ለውጥ ለማምጣት የተያዘውን የ10 ዓመት እቅድ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ ጥሪ የቀረበበት መሆኑን አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር በተካሄደው ጉባዔ የፋይናንስ ብሎም የመሰረተ ልማት አጋርነትን የሚፈጥሩ ውይይቶች ስለመደረጋቸውም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንዲህ ባሉ ዓለም አቀፍ መድረኮች የትውልድ ጥያቄዋ የሆነውን የባሕር በር ጉዳይ በማንሳት፣ ትክክለኛ እና ተገቢነቱን ያሳየች መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፈቲህ፤ በዚህም ጥያቄዋ በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል።
በአፎሚያ ክበበው