በኢትዮጵያ የስፔሻሊቲ ስኮላርሺፕ ዕድልን በመጠቀም የሬዚደንት ሕክምና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎች በአዲስ አበባ የተከናወኑ የከተማ ልማት ኮሪደሮችን፣ የጤና ምርምር ተቋማትን እና የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን ጎብኝተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከጉብኝቱ መርሐ ግብር በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የጤና ዘርፉ ከሀገር ድንበር በላይ የሚያስተሣሥር የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሰው ኃይል ልማትን በማጠናከር የጤና ዘርፍ አቅሟን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራች ነው ያሉት ዶክተር መቅደስ፣ ተማሪዎቹ በቆይታቸው ወቅት የሚያገኙትን ሙያዊ ዕውቀት፣ ልምድ፣ ክህሎት እና የአገልግሎት እሴቶች ወደ ሀገራቸው በመውሰድ ለሕዝባቸው የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያበረክቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ አስተያየት ከሰጡት መካከል ከደቡብ ሱዳን መጥተው በጥቁር አንበሳ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ዶክተር ዩሴፍ ዱት፣ ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት እና የአፍሪካ ኩራት መሆኗን ገልጸው፣ አሁን ደግሞ በልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
ከሶማሌላንድ የዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑት ዶክተር ሲሃም መሐመድ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እየሠሩ ስላሉት አጠቃለይ የልማት ሥራዎች አመስግነዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ሰፊ የከተማ ልማት እና የመሠረተ ልማት ለውጥ እጅግ እንዳስደነቃቸው እና በተመለከቱት አጠቃልይ የልማት ሥራዎች እንደተደሰቱ መግለጻቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።