የሀሳብ ልዩነቶችን እና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ የሥልጡንነት መገለጫ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ቆይተው በሰላማዊ መንገድ ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ጋር በአዳማ ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛል።
ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የቀድሞ ታጣቂዎቹ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ የወሰኑትን ውሳኔ አድንቀዋል።

በሀገራችን ዘላቂ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሰላም መመካከር እና መነጋገር ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኮሚሽኑ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚጀምረው ዋናው ምክክር በተለያዩ ምዕራፎች ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል አሳታፊ እና አካታች የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተሳታፊ ልየታ ሥራ ማከናወኑ ይታወቃል።