ኢትዮጵያ በደማቅ ታሪኳ እየገነባቻቸው ያሉ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የሕዝቧን የማይነጥፍ የልማት ጥማት እና የማይበገር ፅናት በጉልህ የሚያንፀባርቁ ናቸው።
ከእነዚህም ግዙፍ ዐሻራዎች መካከል በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ የሚገነባው አዲሱ ሜጋ አየር ማረፊያ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል። ይህ ፕሮጀክት የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በሚታይ መልኩ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ሐውልት ነው።
ግዙፉ መሠረተ ልማት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ከፍታ በተግባር የሚያረጋግጥ፣ የመንግሥትን የልማት ቁርጠኝነት በሚገባ የሚያሳይ እና የ2040 ሀገራዊ ራዕይን ከዳር ለማድረስ የተዘረጋ እጅግ ጠንካራ ድልድይ ነው።
ከኢትዮጵያ ከፍታ እና ብሔራዊ ጥቅም አንፃር ሲተነተን፣ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ሀገራችን በአፍሪካ ሰማይ ላይ ያላትን የአቪዬሽን የበላይነት በዘላቂነት አስጠብቆ፣ የዓለም የትራንዚት እና የሎጂስቲክስ እምብርት እንድትሆን የሚያደርግ ስትራቴጂያዊ መሣሪያ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከቀረው ዓለም ጋር በማስተሳሰር የሠራው ገድል፣ አሁን ባለው የቦሌ አየር ማረፊያ የቦታ ጥበት እንዳይገደብ ይህ ፕሮጀክት ወቅታዊ ምላሽ ነው። ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 130 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይዞ መነሣቱ፣ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ ብቻ ሳትሆን ዋነኛ መሪ መሆኗን በይፋ ያረጋግጣል።
ይህ ሁኔታ የሀገራችንን ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ጂኦ-ኢኮኖሚያዊ ተሰሚነት በዓለም በማሳደግ፣ ብሔራዊ ጥቅማችንን በማይናወጥ ፅኑ አለት ላይ ይገነባል።

የመንግሥትን ቁርጠኝነት ከማሳየት አኳያ፣ ይህን እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ ግዙፍ ፕሮጀክት አቅዶ ወደ ትግበራ መግባት፣ አመራሩ ለሀገር ሁለንተናዊ ግንባታ ያለውን የማይበገር ፅናት በግልጽ ያሳያል።
በርካታ ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች እና ውስጣዊ ውጣ ውረዶች ባሉበት ፈታኝ ዘመን፣ እንዲህ ባለ የትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለችግሮች እጅ አንሰጥም፤ የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ አናቆምም የሚል ጥልቅ መልዕክት አለው።
መንግሥት ይህንን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ የወሰደው ደፋር እርምጃ፣ የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም ያስቀደመ እና ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር የተከፈለ ታላቅ መሥዋዕትነት ነው። እያንዳንዱ የሚፈስስ ዕውቀት፣ ላብ እና ካፒታል፣ ሀገራችን ከኋላቀርነት ወጥታ በኢኮኖሚ የዳበረች ሀገር እንድትሆን የተያዘውን ፅኑ አቋም ያንፀባርቃል።
የ2040 ራዕያችን ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት፣ በቴክኖሎጂ እጅግ የላቀች እና ዜጎቿ በክብር የሚኖሩባት ሀገር ማድረግ ነው። አዲሱ የቢሾፍቱ የአየር ማረፊያ ከተማ ዘመናዊ የነፃ ንግድ ቀጠናዎችን፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እና የሎጂስቲክስ መንደሮችን አቅፎ በመያዝ ለዚህ ብሩህ ራዕይ መሳካት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ይሆናል።

ይህ ግዙፍ ማዕከል በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል በስፋት ይፈጥራል፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል። የኤክስፖርት ንግዳችንን በማቀላጠፍ አምራቹ ምርቶቹን ከዓለም ገበያ ጋር በሰዓታት ውስጥ በፍጥነት እንዲያገናኝ ሰፊ በር ይከፍታል።
በአጠቃላይ፣ የቢሾፍቱ ሜጋ አየር ማረፊያ የኢትዮጵያ የነገ ብሩህ ተስፋ እና ትንሳኤ ሕያው ማሳያ ነው።
ጥንት አባቶቻችን በደማቸው ነፃነቷን አስከብረው ያቆዩዋትን ሀገር፣ የአሁኑ ትውልድ በልማት እና በሥልጣኔ ከፍ አድርጎ ለማስረከብ እያደረገ ያለው የተግባር ጉዞ ማረጋገጫ ነው።
አዲሱ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ለሀገራችን የብልጽግና፣ የዕድገት እና የዘላቂ ከፍታ የፀና መሠረት በመሆን፣ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በማፋጠን ብሩህ እና የበለጸገች ሀገርን በኩራት ገንብተን ለቀጣዩ እና ለነገው ተተኪ ትውልድ ለማስረከብ የላቀ ታሪካዊ አደራውን ይወጣል።
ይህን ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ሁላችንም በጋራ በመቆም የድርሻችንን መወጣት በታሪክ ፊት ታላቅ ኃላፊነት መሆኑን አጥብቀን መገንዘብ ይኖርብናል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ