ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቢሾፍቱ እየተገነባ ያለውን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ታሪክ ወደር የማይገኝለት ግዙፍ የልማት ሥራ ነው።
ታላቁ ፕሮጀክት በይዞታ ስፋቱ፣ በኢንቨስትመንት መጠኑ እንዲሁም በቦታው ላይ በሚያንቀሳቅሰው አጠቃላይ ማሽነሪ በአፍሪካ ደረጃ ትልቁ መሆኑን አብራርተዋል።
ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ግንባታውን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በልማት ሥራ ላይ ዋናው ቁምነገር የገንዘብ መገኘት ወይም የፕሮጀክቱ ዕቅድ ብቻ ሳይሆን የአፈጻጸም እና የአመራር ብቃት መሆኑን አስምረውበታል።
ባለፉት ጊዜያት በሀገራችን በነበሩ የፕሮጀክት አመራር ክፍተቶች ምክንያት በርካታ ሥራዎች መቼ ተጀምረው መቼ እንደሚያልቁ እንደማይታወቅ አስታውሰዋል።
በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን የማይጠብቁበት እና የሚጓተቱበት ሁኔታ ነበር።
ሆኖም የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ይህንን የተለመደ የአሠራር ታሪክ በዘመናዊ መንገድ የሚቀይር መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በስፍራው ከ8 ሺህ በላይ ሠራተኞች ሌት ተቀን እየሠሩ እንደሚገኙ እና ከ3 ሺህ 8 መቶ እስከ 4 ሺህ የሚጠጉ ግዙፍ ማሽነሪዎች እና ተሽከርካሪዎች በ30 ኪሎሜትር ክበብ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ይህ እንቅስቃሴ በራሱ አንዲት ትንሽ ከተማን እንደሚያክል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ማሽኖቹ በቀን ከ650 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ እንደሚጠቀሙ እና በዐሥር ቀናት ውስጥ ብቻ እስከ 7 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እንደሚያስፈልጋቸው በዝርዝር አስረድተዋል።
ይህንን እጅግ ግዙፍ ሀብት፣ የሰው ኃይል እና ተሽከርካሪ በዘመናዊ መንገድ ማስተዳደር የራሱን የቻለ ከፍተኛ ጥበብና ሥርዓት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ፕሮጀክቱ በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ቁጥጥር እየተመራ ይገኛል።
አጠቃላይ የሥራው እንቅስቃሴ ከመቆጣጠሪያ ክፍል (Situation Room) በቨርቹዋል መንገድ እና በድሮኖች አማካኝነት በቅርበት ክትትል እንደሚደረግበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ከየት ተነሥቶ የት እንደሚቆም፣ በቀን ምን ያህል አፈር እንደሚያመላልስ እና ሥራው ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በዳሽቦርድ (Dashboard) መረጃ እየተሰበሰበ እንደሚተነተን ገልጸዋል።
መንግሥት ይህንን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ፣ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችንም በተመሳሳይ ፍጥነት እና ቴክኖሎጂን በታገዘ መንገድ በማከናወን የሕዝብን የእርካታ ደረጃ ከፍ ለማድረግ አዲስ የፕሮጀክት አስተዳደር አቅም እየፈጠረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በለሚ ታደሰ