የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ የክብር እና የብቃት ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ተገኝተው ግንባታውን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲታሰብ ጀምሮ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬ እንደነበር ጠቅሰዋል።
"ፕሮጀክቱ አይሳካም፤ ይህን የሚያህል ገንዘብ አይገኝም፤ እንዲሁም ይህንን ግዙፍ ሥራ መምራት አይሆንላችሁም" የሚሉ አፍራሽ እሳቤዎች በስፋት ሲስተጋቡ እንደነበር አስታውሰዋል።
አፍራሾቹ ከራሳቸው አቅም እና ዕይታ አንጻር ሲመዝኑት ማሰባቸው እውነት ሊሆን ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሆኖም ኢትዮጵያውያን ይህንን ግዙፍ ሥራ ለማከናወን አቅሙ፣ ዕውቀቱ እና ቁርጠኝነቱ እንዳላቸው በማረጋገጥ ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል።
ይህ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በሀገራችነን እንደነበሩት ፕሮጀክቶች ሳይሆን፣ በከፍተኛ ክትትል የሚመራ መሆኑን ገልጸው፣ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ቃል ገብተዋል።
በሥራው ሂደት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ በርካታ ፈተናዎችን በቅርበት በመከታተል እና በመፍታት ፕሮጀክቱን ወደ ስኬት ማድረስ ዋነኛ ግብ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም አቅም ማሳያ መሆኑን በአጽንኦት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አፍሪካ ማሰብ፣ ማቀድ እና በራሷ አቅም ሠርታ መጨረስ እንደምትችል ለዓለም ማሳያ የሚሆን እና አህጉሪቱን በሙሉ የሚያነቃቃ ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ደረጃ የሚታሰቡ መሰል ግዙፍ ሐሳቦች ወደ ተግባር ሲቀየሩ፣ በገንዘብም ሆነ በዕውቀት ስም ጣልቃ በመግባት ሥራውን ወደኋላ ለማስቀረት የሚሞክሩ አካላትን በጥንቃቄ መከታተል እና መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ፕሮጀክቱ ጊዜው ሲደርስ ማን አሸናፊ እንደሚሆን በተግባር የሚያሳይ እና የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን አቅም በተጨባጭ የሚያረጋግጥ አንጸባራቂ ድል እንደሚሆን በሙሉ መተማመን አብስረዋል።
በለሚ ታደሰ