የቢሾፍቱ አዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለኢትዮጵያ፣ ለአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ እንዲሁም ለመላው ምሥራቅ አፍሪካ ታላቅ በረከት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ተገኝተው ግንባታውን ሲጎበኙ ባደረጉት ንግግር፣ ለፕሮጀክቱ መሳካት መኖሪያቸውን እና የእርሻ ቦታቸውን ለለቀቁ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለሀገር ልማት ሲሉ ላደረጉት ተወዳዳሪ የሌለው አስተዋጽኦ መንግሥት ከፍተኛ ክብር እንዳለው ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም በሀገራችን እንደነበረው ልማዳዊ አሠራር አርሶ አደሩን ከመሬቱ አፈናቅሎ በችግር ላይ የሚጥል ልማት አሁን እንደማይኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
ይልቁንም መቶ በመቶ የነዋሪዎቹ ሕይወት መሻሻሉን እርግጠኛ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋቱን አብራርተዋል።
ለተነሺ አርሶ አደሮች ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን እና የተለያዩ የቢዝነስ ተቋማትም እየተሠሩላቸው መሆኑን በመጥቀስ፣ ልማቱ ሁሉንም ሰው የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ ባለመሆኑ ማኅበረሰብን ማዕከል ያደረገ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህ ፕሮጀክት አፍሪካ በራሷ አቅም ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት እንደምትችል ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ሀብት ወደ አህጉሪቱ የሚያመጣ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ግዙፍ ሥራ በቅርበት ለሚመራው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር ለሚገኘው ስቲሪንግ ኮሚቴ፣ ለቦርድ አባላት፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጅመንት እንዲሁም ድጋፍ ለሚያደርጉ ወዳጆች ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክትም የኢትዮጵያን ድህነት ለመስበር፣ የጥላሸት ማንነትን ለመቀየር እንዲሁም የበለጸገች እና ያደገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማውረስ ሁሉም በተባበረ ክንድ፣ በአንድ ልብና መንፈስ አብሮ እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ከሥራ እና ከልፋት ውጭ ቁጭ ብለን በማውራት የምናመጣው ውጤት እንደሌለ አበክረው በመግለጽ፣ ሁሉም ሀብቱን እና ጉልበቱን አቀናጅቶ ለሀገር ግንባታ እንዲሰለፍ አሳስበዋል።
በለሚ ታደሰ