Search

የቅድመ ሰው አመጣጥን የሚያሳይ አዲስ ግኝት ይፋ ተደረገ

Aug 13, 2025

እስካሁን የትም ያልተገኘ አዲስ የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያ በኢትዮጵያ ማግኘቱን የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ቡድን ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።

ስለሰው ልጅ አመጣጥ የሚያስረዳው እና የሆሞ አባል የሆነው ቅሪተ አካል በአፋር ክልል፣ ለዲ ገራሩ በተባለ ስፍራ መገኘቱ ነው የተገፀው።

በቅርስ ፍለጋው ላይ ባሮኦ መሀመድ አሊ፣ መሀመድ አህመዲን ሀይዳራን ጨምሮ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች እና ድጋፍ ሰጪዎች መሳተፋቸው ተገልጿል።

የተመራማሪዎች ቡድኑ አባላት ግኝቱን በተመለከተ ዛሬ በአዲስ አበባ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ ዝርዝር መረጃውም በዓለም አቀፉ የሳይንስ መጽሔት ኔቸር ታትሞ ወጥቷል።

በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የተመራው የለዲ ገራሩ የምርምር ፕሮጀክት ከእስካሁኖቹ ግኝቶች በዕድሜ ትልቁ ያለውን የሆሞ አባል ቅሪተ አካል ማግኘቱን ነው ያስታወቀው። በተጨማሪም በዓለም ላይ እስካሁን ከተገኙት ሁሉ የላቀ ዕድሜ ያላቸውን የድንጋይ መሳሪያዎች ማግኘቱንም ገልጿል።

የተመራማሪዎች ቡድኑ አባላት ግኝቱን በተመለከተ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አዳራሽ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፥ 13 ጥርሶችን ያካተተው ግኝት በዓይነቱ አዲስ እና እስካሁን ስለሰው ልጅ አመጣጥ የነበረንን አስተሳሰብ የሚቀይር ነው ብለዋል።

የሰው ዝግመተ ለውጥ ከጦጣ ወደ ኒያንደርታል ከዚያም ወደ ዘመናዊ ሰው እያለ ስለመምጣቱ የነበረንን እምነት የሚያፋልስ ነው ብለዋል።

ከአውስትራሎፒቲከስ አፋሬንሲስ (ሉሲ) የተለየ አዲስ ዝርያ መሆኑ የተነገረለት ግኝቱ አውስትራሎፒቲከስ እና የሆሞ አንጋፋዎች በአፍሪካ በአንድ ቦታ እና በተመሳሳይ ወቅት (ማለትም ከ2.6 እስክ 2.8 ሚሊዮን ዓመታት በፊት) አብረው መኖራቸውን ያመላክታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፥ ግኝቱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን በማስረገጥ እንዲሁም የሰው ልጅ አመጣጥን በመረዳት ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።

ቅሪተ አካሉ ስም እንዳልወጣለት የተጠቀሰ ሲሆን፤ ተመራማሪዎቹ ወደመካነ ቅርሱ በቅርቡ በመመለስ ተጨማሪ ቅሪተ አካላትን ለማግኘት ፍለጋቸውን እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።

በመሐመድ ፊጣሞ

#EBC #EBCdotstream #Ethiopia #fossils #humanevolution