ኢቢሲ በራሱ አቅም ያበለፀገው የሞባይል መተግበሪያ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ የሚሆን እንደ ሀገር የተያዘው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ጉዞ አካል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ ገለጹ።
ዳይሬክተሩ ከኢቢሲ ዜና 57 ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢቢሲ አብዛኛውን የሚዲያ ታሪክ ሰንዶ ያስቀመጠ አንጋፋ ተቋም ነው፤ አሁን ላይ ደግሞ ዘመኑ ለሚፈልገው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ትኩረት መስጠቱ ተቋሙ የሄደበትን ርቀት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የሚዲያ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የመንግሥት ተቋማትም ከኢቢሲ ትምህርት በመውሰድ ዘመኑ የሚፈልገውን ዲጂታል ቴክኖሎጂ በራስ አቅም ለማበልፀግ መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
ዘመኑ የደረሰበት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ሥራን የሚያቀል እና የፈጠራ አቅምን የሚጨምር በመሆኑ፤ ኢቢሲ በዲጂታል ዘርፍ እየፈፈጠረው ያለው ንቅናቄ በሀገር ዕድገት ላይ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ሚዲያዎች ሕዝብን እና ትውልድን በመቅረጽ ጉልሕ አስተዋጽኦ አላቸው፤ ኢቢሲ ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ትኩረት መስጠቱ ለትውልዱ ምን ያሕል እየቀረበ እንደመጣ ማሳያ ነው ብለዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ