እጅግ ፈጣንና በአንድ ጊዜ ለ24 የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት መስጠት የሚችለው ዘመናዊ የኃይል መሙያ ጣቢያ በቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተመረቀ።
ይህ ግዙፍ ጣቢያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ባደረገው ትብብር የተሠራ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው እንደገለጹት ተቋሙ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳለጥ ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በኮተቤ፣ ለቡ እና ፒያሳ ሥራ የጀመሩ ጣቢያዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ በቅርብ ወራት ውስጥ በቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ባቱ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ እና ሐዋሳ ከተሞች ተመሳሳይ ጣቢያዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆኑ አብስረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በሀገራችን እየጨመረ መምጣቱን ታሳቢ በማድረግ ለተሠራው የኃይል መሙያ ጣቢያ ምስጋና አቅርበዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በረኦ ሀሰንም፣ ይህ ትብብር የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ አረንጓዴ ልማት ለማሸጋገር ለተያዘው ግብ ትልቅ መሠረት መሆኑን ገልጸው የሚኒስቴሩን ሙሉ ድጋፍ አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገራችን የገቡ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ቁጥር 140 ሺህ የደረሰ ሲሆን፣ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት በአዲስ አበባ 32 እንዲሁም በክልል ከተሞች 8 በድምሩ 40 የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት እየተሠራ ይገኛል።
ከምረቃው መርሐ ግብር ጎን ለጎንም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በአባዲ ወይናይ



