Search

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የቡልቡላ ሮቤ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀመሩ

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 38

 

ምንም ዓይነት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሌላቸው ወረዳዎች ግንባታ የማስጀመር ሂደት በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

May be an image of dais and text

 

May be an image of text

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የቡልቡላ ሮቤ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታን በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን፤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት በትምህርት ዘርፉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ የሪፎርም ተግባራት ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀደመው ጊዜ በባለሀብቱና ለግሉ ዘርፍ ብቻ ተትቶ የነበረው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት በዜጎች መካከል ኢ-እኩልነት ይፈጥር እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ይህንን በመሠረታዊነት ለመቅረፍ በተወሰደ እርምጃ ባለፉት ዓመታት ከ34 ሺህ በላይ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

ይህም ለልጆች የወደፊት ዕድገት መሠረት የሆነና የትምህርት ሥርዓቱን የሚያሻሽል እጅግ ወሳኝ የሪፎርም እርምጃ መሆኑንና ውጤቱም በረጅም ጊዜ የሚታይ እንደሆነ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

አያይዘውም ለ2019 የትምህርት ዘመን የሚደርሱ 1 ሺህ 452 ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ባልሆኑ ወረዳዎች ለመገንባት ታቅዶ ግንባታ የማስጀመር ሥራው በከፍተኛ ፍጥነት እየሄደ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ እነዚህ ትምህርት ቤቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በሁሉም ወረዳዎች እንዲገነቡ ሁሉም ክልል በተሰጠው ዕቅድ መሠረት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ  (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በመጻሕፍት አቅርቦት፣ በሞዴል ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ በመምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲሁም በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

እንደ ክልል በዘርፉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ቢሮ ኃላፊው፤ ምንም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሌላቸውን አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ በትምህርት ሚኒስቴር 181 እንዲሁም በክልሉ 181 በጠቅላላው 362 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በተያዘው ዕቅድ መሠረት ከበርካታ ኮንትራክተሮች ጋር በመፈራረም ወደ ግንባታ እየተገባ መሆኑን ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት ክትትል እንደሚደረግ የገለጹት ዶ/ር ቶላ፣ ማኅበረሰቡ ዕድሜያቸው 5 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት አምጥቶ ማስመዝገብ እንዳለበት አስገንዝበዋል።