በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰኔ 11 እና ሰኔ 12/2018 ዓ.ም የሚሰጠው የ2018 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በ201 የፈተና ጣቢያዎች በዛሬው ዕለት መሰጠት ተጀምሯል።
የከተማ አቀፍ ፈተናውን አጀማመር ለመመልከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በዳግማዊ ብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ተመልክተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በአጠቃላይ 86 ሺህ 783 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተመዝግበው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

ፈተናው ሰላማዊ ሆኖ ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ ቀደም ብሎ ኮማንድ ፖስት ከማደራጀት ጀምሮ ልምድ ያላቸው አስፈጻሚዎች፣ አመራሮችና የጸጥታ አካላት በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች መመደባቸውን አስታውቀዋል።
ተማሪዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የማጠናከሪያ ትምህርቶች ከመሰጠታቸው ባሻገር ደረጃውን የጠበቀ የሞዴል ፈተና እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ከኩረጃ ነፃ እንዲሆን ለተማሪዎችና ለፈተና አስፈጻሚዎች ቅድመ ገለጻ (ኦሬንቴሽን) ተሰጥቷል።
በከተማ አስተዳደሩ የ6ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና ላለፉት ሦስት ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ በስኬት መጠናቀቁ ይታወቃል።