Search

ከትምህርት ተደራሽነት ወደ ጥራት ከፍ ያለው የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ

ዓርብ ሚያዝያ 16, 2018 395

ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት በሀገራችን የነበሩ የትምህርት ፖሊሲዎች ዋነኛ ትኩረት ትምህርትን ማስፋፋትና ተደራሽ ማድረግ ላይ ብቻ ነበር።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ100 ቀናት የመንግሥት የስራ አፈጻጸም ግምገማን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ ቀደምት ሥርዓቶችም ትምህርት "ለጥቂት ጎበዞች ብቻ" ነው በሚል እምነት፣ ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና የተማሪዎችን ቁጥር በማሳደግ ላይ አተኩረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም ይህ መጠነ-ሰፊ ማስፋፋት ከጥራት ጋር አብሮ ባለመሄዱ፣ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ የጥራት መጓደል አስከትሏል።
ይህ አሰራር ትምህርት በአቋራጭ ውጤት የሚገኝበትና በስርቆት የሚታለፍበት እንዲሆን መንገድ ከፍቶ አልፏል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም ተማሪዎች "ዕውቀት የሚገኘው በልፋትና በጥናት ነው" የሚለውን መሠረታዊ መርህ እንዲዘነጉ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
አሁን እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ግን የዲግሪን ትክክለኛ ትርጉም ለመመለስ ያለሙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ አንድ ተማሪ ዲግሪ ማግኘት የሚችለው ሰርቶና አውቆ ብቻ እንዲሆን ጥብቅ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
ምንም እንኳ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ጠንከር እንዲል መደረጉ መጀመሪያ ላይ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ አሁን ላይ ግን አዎንታዊ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ተናግረዋል።
ወላጆች ልጆቻቸው በትክክል ተምረው እንዲያልፉ ያላቸው ፍላጎት ሲጨምር፣ ተማሪዎችም ውጤት የሚገኘው በማጥናት መሆኑን በመረዳት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።
በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ክፍት ሆነው ተማሪዎች ሲያጠኑ ማየት የተለመደ ሆኗል።
ይህ አዲስ የትምህርት አቅጣጫ ትውልዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ውድድር መቋቋም እንዲችል ያደርገዋል። እንዲሁም የሀገራችንን የኢኮኖሚ ጉዞ የሚሸከምና ኢትዮጵያ የሚገባትን ትልቅ ሥፍራ በተግባር የሚያረጋግጥ ዜጋ ለመፍጠር በሩን ከፍቷል።
በኢንቲሃድ አብራር