የቻይናው ታዋቂ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጂሊ ለሚያመርታቸው የኤሌትሪክ መኪኖች መረጃ ለመስጠት የሚረዱ 11 ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር ማምጠቁ ታውቋል።
ኩባንያው ለሚሰራቸው መኪኖች ምቹ ፈጣንና አስተማማኝ መረጃ ማቀበል የሚችሉት እነዚህ ሳተላይቶች፣ ከፊት ለፊት የተዘጋጋ መንገድ ሲኖር ቀድመው በማየት ለሾፌሩ በማሳወቅ አማራጭ መንገዶችን እንደሚጠቁሙ ነው የተነገረው፡፡
በተለይ ሰው አልባ ለሆኑ ተሽከርካሪዎች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት አገልግሎቱን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና አላቸው ተብሏል።
የመኪናው ቻርጅ ሲቀንስ በቅርብ የሚገኝ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ በመጠቆም የኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ያሳውቃሉ።
እንደ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲኖሩ አሽከርካሪው አቅጣጫውን እንዲቀይር ወይም እንዲቆም የማሳወቅና የመሳሰሉትን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ቻይና ደይሊ ዘግቧል።
በአለም ላይ ካሉ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የራሱን ሳተላይቶች ወደ ጠፈር የላከው ጂሊ፤ ሰሞኑን የላካቸውን 11 ሳተላይቶች ጨምሮ እስካሁን 41 ሳተላይቶችን የላከ ሲሆን በዚህ ዓመት መጨረሻ 72 የማድረስ እቅድ አለው።
መኪና የማምረት ስራውን ከጀመረ 28 ዓመታት የሆነው የቻይናው ተሽከርካሪ አምራች ጂሊ፣ በአሁኑ ወቅት በዓመት ከ3 ሚሊዮን በላይ ዘመናዊ መኪኖችን እያመረተ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።