Search

ካካዎ እና ማካዴሚያ፡ የአረንጓዴ ዐሻራ አዳዲሶቹ ትሩፋቶች

ዓርብ ሰኔ 12, 2018 68

 

 የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዓላማ የደን ሽፋንን ከማሳደግም በላይ ዓለማ ያለው ነው።

መርሐ ግብሩ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የሥነ-ምህዳር መራቆትን ለመከላከል እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተነደፈ ሰፊ የፖሊሲ መዋቅር ነው።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ከደን ልማት ጎን ለጎን ለምግብ ዋስትና ጠቃሚ የሆኑ ዝርያዎችን የማላመድ እና የመትከል ሰፊ ሥራ ተከናውኗል።

 

በዚህም ከአሥር በላይ ምርጥ የፍራፍሬ ዝርያዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች መጥተው ማላመድ ተችሏል።

 

ከተዋወቁት አዳዲስ ዝርያዎች መካከል ካካዎ እና ማካዴሚያ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ዝርያዎች አካባቢን ከመንከባከብ ባለፈ፣ አርሶ አደሩን የዘላቂ ሀብት ባለቤት ለማድረግ ትልቅ ዓላማ አንግበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሲያስጀምሩ ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

ካካዎ በኢትዮጵያ

ካካዎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ተፈላጊነት ያለው ተክል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ የሆነ ተክል በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት አላምዳለች፡፡

በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር በሚገኘው የቴፒ ምርምር ማዕከል 'ፎራስቴሮ' ዝርያን በተሳካ ሁኔታ አላምዷል።

ይህ የምርምር ውጤት በሄክታር አማካይ 0.58 ቶን ምርት አስመዝግቧል። ይህም ከዓለም አቀፉ አማካይ ምርት መጠን ጋር ሲነጻጸር 45 በመቶ ብልጫ አለው።

ካካዎ ጥላ አፍቃሪ ሰብል በመሆኑ ደን ባለባቸው የቡና አብቃይ አካባቢዎች ከቡና ጋር ተቀላቅሎ የሚለማ ተክል ነው።

ይህም የተፈጥሮ ደንን ሳይነካ እና የአፈርን ለምነት ጠብቆ ብዝኃ ህይወትን ለማበልጸግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ማሳያ ነው።

በዓለም ገበያ አንድ ቶን ካካዎ 8 ሺህ እስከ 12 ሺህ ዶላር ይሸጣል፡፡ በመሆኑም ከቡና በተጨማሪ አዲስ የውጭ ምንዛሬ የገቢ ምንጭ ይሆናል።

በተጨማሪም ለኢንዱስትሪዎች የሚሆን የካካዎ ግብዓትን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ያስቀራል።

ማካዴሚያ፡ ውዱ የለውዝ ዝርያ

በዓለም ላይ እጅግ ውድ ከሆኑ የለውዝ ዝርያዎች መካከል አንዱ የሆነው ማካዴሚያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተጠቀሱት መካከል ነው።

ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የተሻሻሉ ዝርያዎች እስከ 12 ዓመታት ከሚፈጀው ጊዜ በተሻለ 24 ወራት ውስጥ ፍሬ መስጠት ስለሚችሉ፣ አርሶ አደሩን በፍጥነት ተጠቃሚ ያደርጋሉ።

የማካዴሚያ ዛፍ አፈርን አጥብቆ በመያዝ መሸርሸርን ይከላከላል፤ የከርሰ-ምድር ውኃንም ይጠብቃል።

ለቡና ተክሎችም ምርጥ ጥላ በመሆንም ያገለግላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በኪሎ 12 እስከ 15 ዶላር የሚሸጠው ይህ ምርት ለአርሶ አደሮች ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም ይፈጥራል።

እነዚህ አዳዲስ ዝርያዎች ለሥነ-ምህዳር ጥበቃ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነው።

እነዚህ ተክሎች ከምግብነት ጠቀሜታቸው ባሻገር፣ በችግኝ ጣቢያዎች፣ በትራንስፖርት እና በማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ለበርካታ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራሉ።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን ግብርና ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ እያሸጋገረው ይገኛል የሚባለው ለዚህ ነው።

በለሚ ታደሰ