የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላትን ጨምሮ በነሀሴ ወር የሚከበሩ በዓላትን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
በአማራ ክልል በየዓመቱ ከነሀሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና እንግጫ ነቀላ የአደባባይ በዓላት እንደሚከበሩ የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ ለኢቢሲ ተናግረዋል።
“እነዚህ በዓላት በተለይ ልጃገረዶች አደባባይ በመውጣት በድምቀት የሚያከብሯቸው በመሆናቸው የልጃገረዶች የነፃነት በዓላት ናቸው ብሎ መውሰደ ይቻላል” ብለዋል።
በዓላቱ በልጃገረዶች ብቻ ሳይሆን በሌላውም የማኀበረሰብ ክፍል ጭምር ተናፋቂ እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።
ከቀናት በኋላ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች መከበር የሚጀምሩት እነዚህን በዓላትን የማኀበረሰቡን ማኀበራዊ ግንኙነትን እና መስተጋብርን የሚያጠናክሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በተጨማሪም እነዚህ በዓላት የዜጎችን የእርስ በርስ የመጠያየቅ እሴትን የሚያጎለብቱ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ከዚህም ባሻገር በዓላቱ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ማደግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱም ነው የተናገሩት።
ከነሀሴ 16 እስከ 21 ቀን 2017 ዓ.ም የሻደይ፣አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት በስፋት በሚታወቁባቸው በወሎ፣በዋግ ኸምራ እና ሌሎች አካባቢዎች በድምቀት እንደሚከበሩ አሳውቀዋል።
እንዲሁም እንግጫ ነቀላ በዓልን በጳጉሜን ወር የመጨረሻዎቹ ቀናት በምስራቅ ጎጃም አካባቢዎች በድምቀት ለማክበር ዝግጀት እየተደረገ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።
በበዓላቱ ለመሳተፍ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚመጡ ጎብኚዎች ምቹ አገልግሎቶችን ለመስጠት ከሆቴል ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቂ ዝግጅት በማድረግ እንግዶችን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት በተጨማሪም የቡሄ (የደብረ ታቦር) በዓልን በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።
በሳሙኤል ወርቅዓየሁ