በዓለማችን ላይ የሰው ልጅ ጥበብ፣ እውቀት እና ጉልበት ከተፈተነባቸው ታላላቅ የዘመናችን ድንቃድንቆች መካከል፣ ግዙፍ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛሉ።
የሲንጋፖርን ቻንጊ በሚያስደምም ተፈጥሯዊ ውበቱ፣ የመካከለኛው ምስራቁን ዱባይ በንግድ ትስስሩ ወይም የደቡብ አፍሪካውን ኤር ታምቦን ብንመለከት፤ እነዚህ ስፍራዎች የየሀገራቱን የኢኮኖሚ ትርታ እና የቴክኖሎጂ አቅም የሚያስተጋቡ ዘመናዊ ስፍራዎች ናቸው።
ሆኖም ከቢሾፍቱ ከተማ ወጣ ብሎ "አቡሴራ" በተሰኘው ስፍራ እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ ሜጋ አየር ማረፊያ ሲታሰብ፣ ታሪኩም ሆነ ትርክቱ ፈፅሞ የተለየ ይሆናል።
ይህ ፕሮጀክት ከነባሮቹ የአፍሪካ አየር ማረፊያዎች አንፃር ሲመዘን፣ ሌሎችን በብዙ እርምጃ ወደኋላ የሚተው፤ ከዓለም ታላላቅ የአቪዬሽን ማዕከላት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የነገዋን አፍሪካ የብልጽግና ተስፋ በጉልህ የሚያሳይ፣ ኢትዮጵያ በገዛ እጆቿ እያነፀችው ያለ አዲስ የዓለም ድንቅ ነው።
ወደ አቡሴራ ምድር ስንረግጥ የምናየው እውነት እጅግ አስገራሚ እና ልብን በሀገራዊ ኩራት የሚሞላ ነው። ይህ ስፍራ ዛሬ ላይ ተራ የኮንስትራክሽን ቦታ ሳይሆን ኢትዮጵያ አዲስ ተዓምር እያፈለቀችበት ያለ ግዙፍ የልማት ላቦራቶሪ ሆኗል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች፣ መሀንዲሶች እና ልዩ ልዩ ባለሙያዎች እንደ አንድ ልብ መቺ፣ እንደ አንድ ቃል አናጋሪ ሆነው በስፍራው ሌት ተቀን ሲንቀሳቀሱ መመልከት፣ የሰው ልጅ ትጋት እና አገራዊ ፍቅር ተራራን እንዴት እንደሚያንቀጠቅጥ ህያው ምስክር ነው።
ያ ሁሉ ሰራተኛ በግዙፍ እና ዘመናዊ ማሽነሪዎች ታጅቦ፣ አፈሩን ገልብጦ፣ አለቱን ሰንጥቆ የነገዋን የንግድ ገነት ሲያነፅ ማየት፣ አቡሴራን በእርግጥም የኢትዮጵያ "አዲሱ አለም" ያሰኘዋል።

ይህ የእንቅስቃሴ ውቅያኖስ የኢትዮጵያን የማይበገር የህዳሴ መንፈስ በተግባር የሚተረጉም፣ የሀገርን ከፍታ በላብ እና በእውቀት እውን እያደረገ ያለ እጅግ ማራኪ ትዕይንት ነው።
የዚህ ፕሮጀክት ታላቅነት እና ግዙፍነት የሚለካው በፈሰሰበት የካፒታል መጠን ወይም በሚይዘው የስፋት ካሬ ብቻ አይደለም።
በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው፣ በአንድ ጊዜ አራት ግዙፍ ማኮብኮቢያዎችን እንዲሁም እጅግ ዘመናዊ የነፃ ንግድ ቀጠናዎችን የሚያስተናግደው ይህ ማዕከል፣ አፍሪካን ከዓለም ጋር የሚያስተሳስር ቁልፍ የደም ስር ነው።
የግብፁን ካይሮ፣ የሞሮኮውን ካዛብላንካ ወይም የኬንያውን ጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያዎችን በብዙ እጥፍ ርቀት የሚያስከነዳው አቡሴራ፣ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ታሪካዊ የበላይነት ወደ ፍፁም የማይገደደር ደረጃ ያሸጋግረዋል።
ይህ የአቡሴራ ተዓምር ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ እጅግ ትልቅ የሚያደርግ፣ ሉዓላዊ ክብሯን በጠንካራ የኢኮኖሚ ጡንቻ የሚያስጠብቅ ብሔራዊ የኩራት ምንጭ ነው።
አቡሴራ ላይ እየተገነባ ያለው ተራ የአስፋልት ንጣፍ እና የብርጭቆ ህንፃ ሳይሆን ሀገራችን በዓለም አቀፉ የንግድ፣ የቱሪዝም እና የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ የመደራደር አቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ፅኑ አለት ነው።

ትናንት በታሪክ ገፆች ስሟ በጀግንነት ሲነሳ የነበረችው ሀገር፣ ዛሬ ደግሞ አቡሴራ ላይ በሚታየው የስራ ክንውን አማካኝነት የስልጣኔ እና የዘመናዊነት ተምሳሌት እየሆነች ነው።
በድካም፣ በላብ እና በረጅም ርቀት ራዕይ እየታነፀ ያለው ይህ ግዙፍ የአቪዬሽን ከተማ፣ ኢትዮጵያ ለትውልዶች የምታወርሰው የማይነጥፍ የሀብት ማመንጫ ነው።
በዓለም ሰማይ ላይ ደምቆ የሚበራ የብልጽግናችን አዲስ ኮከብ በመሆን፣ ዜጎቿን በኩራት የሚያስኮራ ትልቅ ሀገራዊ ሀውልት ነው።
አቡሴራ በእርግጥም የኢትዮጵያ የከፍታ ማማ፣ ለዓለም የምትከፍተው ሰፊ እና ዘመናዊ በሯ፣ እና ከተፈጠሩት ተዓምራቶቿ ሁሉ ቁንጮ የሆነ የዘመናችን "አዲሱ አለም" ነው!

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ