የተራቆቱ ተራሮቿን በአረንጓዴ ካባ እያለበሰች የምትገኘው ሀገራችን፣ ተፈጥሮን ከማዳን በዘለለ የዜጎቿን የዕለት ጉርስ ዋስትና ወደምታረጋግጥበት አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ ተሸጋግራለች።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሲነሣ በአብዛኛው ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የአካባቢ ውበት እና የተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ ቢሆንም፣ ከዚህ ሥነ ምኅዳራዊ እሳቤ በስተጀርባ እጅግ ረቂቅ የሆነ የኢኮኖሚ ሽግግር እና የምግብ ዋስትና ትሥሥር ይገኛል።
ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ "ከጥላ ማግኘት ወደ ኪስ ማዳበር" እንዲሁም "ከጓሮ ውበት ወደ ማዕድ መሙላት" የተደረገ ታላቅ የግብርና እና የኢኮኖሚ ሽግግር ነው።
የፍራፍሬ ተክሎች አብዮት እና የተመጣጠነ ምግብ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ከሌሎች የተለመዱ የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች በእጅጉ የሚለየው፣ በጥምር ግብርና እና በፍራፍሬ ተክሎች ላይ ባደረገው ስትራቴጂያዊ ትኩረት ነው። ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ከተተከሉት ጠቅላላ የችግኝ ዓይነቶች ውስጥ ከ55 በመቶ በላይ የሚሆነው የጥምር ግብርና እና የፍራፍሬ ተክሎችን ያካተተ ነው።
ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓያ እና የአፕል ችግኞች መተከላቸው የዜጎችን የምግብ ሥርዓት ከመቀየር ባለፈ፣ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ ይገኛል።

ቀደም ሲል ለጥላ ወይም ለማገዶ ብቻ ዛፍ ይተክል የነበረው አነስተኛ አርሶ አደር፣ አሁን በከፍተኛ የገበያ ዋጋ በሚሸጡ የፍራፍሬ ዛፎች እና መደበኛ ሰብሎች አቀናጅቶ በመትከል የዕለት ገቢውን በማሳደግ የምግብ ዋስትናውን በራሱ አቅም እያረጋገጠ ነው።

የአፈር ጤንነት እና የውኃ በረከት
የምግብ ዋስትና ያለ ጤናማ አፈር እና በቂ የውኃ አቅርቦት ሊታሰብ አይችልም። በደጋማ እና ተዳፋት አካባቢዎች በስፋት የተተከሉት ችግኞች የጎርፍ መሸርሸርን በመከላከል የላይኛውን ለም አፈር በቦታው እንዲቆይ አድርገዋል። ተክሎቹ የሚያረግፉት ቅጠል ደግሞ ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት (Compost) በመቀየር የአፈሩን ለምነት ይጨምራል።
ከዚህም በተጨማሪ ከ10 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የተራቆተ መሬት እና ተፋሰስ በችግኞች መሸፈኑ የከርሰ ምድር ውኃ መጠን እንዲጨምር እና የደረቁ ምንጮች ዳግም እንዲመነጩ አድርጓል። ይህ ቀጥታ ትሥሥር ለግብርና ምርታማነት ማደግ፣ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና በአጠቃላይ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጽኑ መሠረት ነው።

ከኤክስፖርት ገቢ እስከ አግሮ-ኢንዱስትሪ ትሥሥር
የአረንጓዴ ዐሻራው የምግብ ዋስትና ስኬት በኤክስፖርት እና በኢንዱስትሪ ትሥሥርም በጉልህ ይታያል። ኢትዮጵያ ለዘመናት በቡና እና በጥራጥሬ ኤክስፖርት ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና የቆየች ቢሆንም፣ አሁን ግን ይህ ታሪክ በአረንጓዴ ዐሻራ የፍራፍሬ ምርቶች እየተቀየረ ነው።
በተመሳሳይ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት ወደ ውጭ ይላክ የነበረውን 230 ሺህ ቶን የቡና ምርት በአረንጓዴ ዐሻራ በተሠራው ጠንካራ ሥራ አሁን ላይ ወደ 475 ሺህ ቶን በማሳደግ ሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ አድርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ምርቶች በቀጥታ ለምግብነት ብቻ ሳይውሉ ለሀገራችን የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረት እየሆኑ ነው።
በይርጋለም፣ ቡሬ እና ኮምቦልቻ ለተቋቋሙ የፍራፍሬ ጭማቂ እና የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ዋነኛ የጥሬ ዕቃ ምንጭ የሆኑት ይኸው የአረንጓዴ ዐሻራ ውጤቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እያከናወነችው ያለው ታላቅ ሥራ የዛፍ ተከላ ብቻ ሳይሆን የሕይወት እና የሕልውና መሠረት ነው። ዛሬ የምንተክለው እያንዳንዱ የፍራፍሬ ችግኝ እና የምንከባከበው ደን የነገዋን ማዕድ የሚሞላ፣ ድርቅን የሚቋቋም፣ የኢንዱስትሪ ግብዓትን የሚያቀርብ እና የሕዝባችንን የምግብ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ሕያው ዋስትና ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ