Search

የሉዓላዊነት ዐለት

ዓርብ ሰኔ 12, 2018 103

 

የኢትዮጵያ  መከላከያ ሠራዊት እውነተኛው አስፈሪው የሉዓላዊነት ዐለት ነው። ይህ ሠራዊት ከታጠቀው ጠመንጃ ኃይል እና ከውጊያ ብቃት በበለጠ፣ በውስጡ በሰረጸው ጥልቅ ፍልስፍና፣ የሀገር ፍቅር ራዕይ እና የሀገር አገልጋይነት ረቂቅ እሳቤ የተሠራ ድንቅ ተቋም ነው።

የተፈጠረበት፣ ሌት ተቀን የሚጋደልበት እና መሥዋዕት የሚሆንበት ብቸኛ ዓላማውም የኢትዮጵያን ዘላለማዊነት፣ ክብር እና የሕዝቦቿን ፍጹም ደኅንነት ማረጋገጥ ብቻ ነው።

ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ በከፍተኛ የልህቀት ደረጃ ለማሳካት ደግሞ የቅርብ ጊዜው ተቋማዊ ሪፎርም መዋቅራዊ ማሻሻል ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም ሠራዊቱን በሀገራዊ ሥነ-ልቦና፣ በንፁህ ኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ እና በዘመናዊ ሳይንሳዊ ወታደራዊ እውቀት በማነጽበድጋሚ ፈጥሮታልማለት ይቻላል።

የሠራዊቱ የእሳቤ ግንባታ ማዕከል ዋነኛ ተግባር፣ እያንዳንዱን ወታደር እና መኮንን ከብሔር አጥር፣ ከወገንተኝነት እና ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትኩሳት አውጥቶ፣ ሙሉ በሙሉ ለአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ብቻ የሚታዘዝ የኅሊና ቁንጮ ማድረግ ነው።

ይህ የአስተሳሰብ ግንባታ ሠራዊቱን በማንኛውም የፓለቲካ ማዕበል እና ሽንገላ የማይበገር፣ ከጥርጣሬ እና ከመከፋፈል የጠራ እና ለሰንደቅ ዓላማው ብቻ ታማኝ የሆነ ኃይል አድርጎታል።

ወታደሩ ወደ ጦር ግንባር ከመሰማራቱ በፊት በውስጣዊ ሥነ-ልቦናው ውስጥ የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የታሪክ አደራ እና የሕዝብ ፍቅር በፅኑ የሚቀረጽበት ይህ የእሳቤ ማዕከል፣ ከተራ ተዋጊነት ወደ የሀገር ጠባቂነት ያሻገረው ድንቅ መዋቅር ነው።

ይህ ሥራ ሠራዊቱ የሀገር ፍቅርን እንደ ትጥቅ እንዲለብስ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት የሀገር አገልጋይነቱ በሥልጠና ብቻ ሳይሆን በኅሊና እምነት የጸና ሆኗል።

ይህ አስደናቂ ተቋማዊ ሥሪት ከአባቶቹ የወረሰው የታሪክ እና የጀግንነት ሕያው ቀጣይነት ነው። የኢትዮጵያ መከታ ሠራዊት አባቶች ለሀገራቸው ነፃነት እና ክብር በየዱር በገደሉ፣ በበረሃው እና በሐሩሩ የከፈሉትን ታላቅ መሥዋዕትነት፣  ያሳዩትን ፍጹም ወኔ በደሙ ውስጥ ሰንቆ የያዘ ኃይል ነው።

ነገር ግን ይህንን ከአያት ቅድመ-አያቶቹ በውርስ ያገኘውን የተፈጥሮ ጀግንነት፣ በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ፣ በስትራቴጂያዊ ዕውቀት እና በረቀቀ ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ልዩ ተቋማዊ መልክ ሰጥቶታል።

የአባቶች ወኔ እና የዘመኑ የቴክኖሎጂ ልህቀት በአንድነት ሲዋሃዱ፣ ሠራዊቱን በማንኛውም ወራሪ እና የውስጥ ጠላት ፊት የማይደፈር እና የማይደነግጥ ፅኑ የሉዓላዊነት ጋሻ አድርገውታል። የጀግንነት ምንጩ የታሪክ ውርስ ሲሆን፣ አወቃቀሩ ግን ዘመናዊ እና ሥልጡን ነው።

መከላከያ ሠራዊቱ በታሪክ ጉዞው ውስጥ ከፊቱ የተጋረጡበትን እጅግ አስፈሪ እና ውስብስብ ፈተናዎች፣ የውስጥ ክህደቶች እና ውጫዊ ጫናዎችን ሁሉ በቀላሉ እየተረማመደባቸው እዚህ የደረሰው በዚህ የላቀ ሥሪቱ እና ፅኑ የውስጥ እሳቤው ምክንያት ነው።

ተቋሙን ለማፍረስ እና ሀገርን ለመበተን የታለሙትን ታላቅ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ሴራዎች በብቃት በመቀልበስ፣ የኢትዮጵያን ትንሣኤ እና ሕልውና አስተማማኝ አድርጓል።

ሠራዊቱ በፈተናዎች ውስጥ ሲያልፍ አልደከመም፤ ይልቁንም ይበልጥ እየጠነከረ፣ ራሱን እያደሰ እና አቅሙን እያጎለበተ ወጥቷል። ዛሬ ላይ መከላከያ ሠራዊታችን የጦር ሜዳ ጀግና ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብ አለኝታ፣ በልማት ግንባር-ቀደም የላብ ዐርበኛ እና የኢትዮጵያ የማይናወጥ የክብር መተማመኛ ምሰሶ ነው።

የሠራዊቱ እንደገና መገንባት እና የአስተሳሰብ አድማስ መለወጥ፣ ሀገራችን በፈታኝ የታሪክ ማዕዘናት ላይ ስትደርስ በቅጽበት መፍትሔ እንድታገኝ አስችሏታል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሥሪት እና የእሳቤ ግንባታ ፍሬ፣ በለውጥ የታደሰ፣ በእውቀት እና በቴክኖሎጂ የበለጸገ፣ በዲሲፕሊን የታነጸ እና ሀገርን ወደ ብልጽግና ከፍታ ለመውሰድ ቆርጦ የተነሣ የማይበገር ኃይል ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ