2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከመጪው ጳጉሜ 03 እስከ 05/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል ።
ፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የጉባዔውን ዝግጅት አስመልክቶ ከፌዴራል አስተባባሪ እና ከግሉ ሴክተር የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።
በወቅት የፕላንና እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ለጉባዔው ስኬት የግሉ ሴክተር ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በጉባዔው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል እየወሰደች ያለቻቸው እርምጃዎች ይቀርባሉም ያሉ ሲሆን፤ አፍሪካ እንደ አህጉር እያደረገች ያለውን አስተዋጽኦም ለዓለም የሚገለጥበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በኤሌክትሪክ በትራንስፖርት እና በሌሎች ዘርፎች የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ያላት ተሞክሮ በጉባዔው ላይ ይቀርባልም ተብሏል።
እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በግልጽ ማሳየት እና ቀጣይነት ባለው መልኩ የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ፤ ሀገራት በጋራ ድምፅ የሚያሰሙበት እንደሆነ ተገልጿል።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ አነስተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ የምትፈጥር አህጉር ብትሆንም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባታል።
ስለሆነም ጉባዔው ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የገቧቸውን ቃሎች በተግባር እንዲያሳዩ እና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ምንጭ እንዲዘረጋ ትኩረት የሚሰጥበት ይሆናልም ተብሏል።
ጉባዔው "ዓለም ዐቀፍ የአየር ንብረት መፍትሔዎችን ማፋጠን ፣ የአፍሪካ የማይበገር እና አረንጓዴ ልማት ፋይናንስ መደገፍ" በሚል መርሕ ነው የሚካሄደው።
በትዕግስቱ ቡቼ