Search

የፕሬዚዳንት ዜለንስኪ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር የለንደን ውይይት

ሓሙስ ነሐሴ 08, 2017 155

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር በለንደን ዳውኒንግ ስትሪት ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በዛሬው እለት ዘለንስኪ ዩናይትድ ኪንግደም ሲደርሱ በጠቅላይ ሚንስትር ስታርመር ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ቢቢሲ ዘግቧል።

ሁለቱ መሪዎች የተገናኙት ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን በአላስካ ከሚያደርጉት ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።

ስታርመር በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተኩስ አቁም ለመፍጠር "እውነተኛ ዕድል" እንዳለ ከአሜሪካ - ዩክሬን ስብሰባ በፊት ጠቁመዋል።

ዜለንስኪ በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬንን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን የገለፁ ሲሆን፤ የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ ደግሞ የሰላም ስምምነት ካልተደረሰ በፑቲን ላይ የበለጠ ጫና እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

ዘሌንስኪ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ከተገናኙ በኃላ ለመገናኛ ብዙሃን ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጡም።

ወሳኙ ስብሰባ ትራምፕ እና ፑቲን ሲገናኙ የሚደረግ ቢሆንም ስታርመር እና ዘሌንስኪ ውይይቱ አካል አለመሆናቸው ነው የተገለፀው።

በትራምፕ እና በፑቲን መካከል በነገው እለት የሚካሄደው ውይይት በዩክሬን እና በአውሮፓ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል ተብሏል።

 

በሴራን ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #UK #EU