ኢትዮጵያ ስልታዊ ኢንቨስትመንቶችን እና ጉልህ ማሻሻያዎችን በተግባር ላይ በማዋል፣ የግብርና ዘርፉ ከነበረበት "ከእጅ ወደ አፍ" ልማድ በማላቀቅ ከእርሻ ወደ ንግድ ብሎም ወደ የምግብ ሉዓላዊነት መሠረትነት ማሸጋገሯን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ ታከናውናለች” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ላይ የዘርፉን የለውጥ ጉዞ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ይህ ሽግግር ዕውን ሊሆን የቻለው ከ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ ጋር የተጣጣሙ ስትራቴጂዎችን እና አዳዲስ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ተግባራዊ በማድረግ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ የግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ምርታማ፣ በገበያ ላይ የተመሠረተ እንዲሁም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ቀውሶችን የመቋቋም አቅሙ የዳበረ ሊሆን የቻለው በሚከተሉት ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች ነው።
አጋርነትን ማጠናከር፦ የመንግሥት፣ የግል ዘርፉን እና የሕዝብ አጋርነትን በማስተሳሰር፤
ፈጠራ እና ቢዝነስ፦ በዘርፉ አዳዲስ ፈጠራዎችን እና የግብርና ቢዝነስን (Agribusiness) በስፋት በማበረታታት፤ እንዲሁም
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፦ ቴክኖሎጂን እና የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በግብርናው ሥርዓት ውስጥ በማካተት ነው።
በተጨማሪም ቀደም ሲል ሀገራችን ከውጭ በሚገቡ የግብርና ምርቶች ላይ በስፋት ተመርኩዛ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ማንደፍሮ፣ አሁን ላይ ግን በሀገር ውስጥ ተተኪ ምርቶችን በማሳደግ በኩል አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም እንደ የሌማት ትሩፋት ያሉ ሀገር በቀል ተነሣሽነቶች ሀገራችን በምግብ ራሷን እንድትችል ከማድረጋቸውም ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑን አስረድተዋል።
እነዚህ የታቀዱ እና መጻኢውን ጊዜ ያገናዘቡ ስልታዊ እርምጃዎች ለዘላቂ የግብርና አብዮት፣ ለገጠር ብልጽግና እና ለጠንካራ ኢኮኖሚ አስተማማኝ መሠረት እየጣሉ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ይህም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኗን በተግባር የሚያሳይ ነው ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።