የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ "ቅጠል ተራ" በተባለ አካባቢ ከሁለት ወራት በፊት ያስጀመረው የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እጅግ አበረታች በሆነ ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባዋ ዛሬ በግንባታ ስፍራው ተገኝተው የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በገመገሙበት ወቅት እንደገለጹት፣ የዛሬ ሁለት ወር ግንባታቸው የተጀመሩ ሕንፃዎች በአሁኑ ወቅት 9ኛ ወለል ላይ ደርሰዋል።

ቦታውን ከማጽዳት ጋር በተያያዘ የዛሬ ወር የተጀመሩ ሕንፃዎች 4ኛ እና 5ኛ ወለል ላይ መድረሳቸውን፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በፕሮጀክቱ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርገው የተጨመሩት ሦስት ተጨማሪ ሕንፃዎች ግንባታም በጥሩ ጅማሮ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
እንደ ከንቲባ አዳነች ማብራሪያ፣ ይህ ፕሮጀክት መኖሪያ ቤቶችን ከመገንባት ባለፈ የተቀናጀ የከተማ ልማትን ያማከለ ነው። በሥፍራው ከቤቶቹ በተጓዳኝ የንግድ ማዕከላት፣ የጸጥታ እና ደኅንነት፣ የትምህርት እና የጤና ተቋማት እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ እና የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች እኩል ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተገነቡ ይገኛሉ።

"የምንገነባው መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን፣ ሕፃናት ቦርቀው የሚያድጉበት፣ ወጣቶች ብቃታቸውን የሚያዳብሩበት፣ ዜጎች አገልግሎቶችን በቅርበት የሚያገኙበት እና ክብራችንን የሚያስጠብቅ ምቹና ጽዱ አካባቢን ነው" ሲሉ ከንቲባዋ የፕሮጀክቱን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አስረድተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ይህንን የቅጠል ተራ መኖሪያ መንደር፣ በቅርቡ ግንባታው ከተበሰረው "ገዳም ሰፈር" እና በመሐል ከሚገኘው "ጣልያን ሰፈር" ጋር በማስተሳሰር እና በማልማት፣ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ የዘመነ አኗኗር ሥርዓት የሰፈነበት እና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ማዕከል ለማድረግ ማቀዱም ተጠቁሟል።
በምርጫ ወቅት ላይ ሆነን የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሳይቀዛቀዝ መቀጠሉ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ነዋሪዎቻችንን በታማኝነት የማገልገል አቋማችን ፅኑ መሆኑን ያሳያል ብለዋል ከንቲባዋ።
ሕንፃዎቹን በጥራት እና በፍጥነት ገንብተው በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ርብርብ እያደረጉ ለሚገኙ አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ ማኅበራት፣ ተቋራጮች እና አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።