7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተጠናቅቆ የሕዝብ እንደራሴዎች ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ሲገቡ፣ የሀገራችን የፖለቲካ ትኩረት ከምርጫ ዘመቻ ወደ ተግባራዊ የሀገር ግንባታ ምዕራፍ ይሸጋገራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበሻሻ የምርጫ ጣቢያ ድምፃቸውን በሰጡበት ወቀት ያስተላለፉት አንድ ወሳኝ መልዕክት “እኔን ዛሬ የሚያሳስበኝ መራጩ ሳይሆን ተመራጩ ነው” የሚል ነበር፤ ይህ መልዕክት የፖለቲካው ሸክም አሁን ሙሉ በሙሉ በሕዝብ እንደራሴዎች ትከሻ ላይ መውደቁን የሚያስገነዝብ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ያስተላለፉት ጠንካራ መልዕክት በፓርላማ ወንበር ላገኙ ተመራጮች በሙሉ፣ የገዢም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ አባል ሳይል፣የተሰጠ የጋራ ሀገራዊ የኃላፊነት ማዕቀፍ ነው።
ሕዝብ የዜግነት ግዴታውን ተወጥቶ ድምፁን ሰጥቷል፤ አሁን ኳሷ ያለችው በተመራጮች ሜዳ ላይ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳሰቢያ መነሻ በማድረግ ስንመለከት ሁሉም ተመራጮች በአንድነት የተሸከሙት ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት አለ።
ከእነዚህም ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው የሞራል ልዕልና ነው፤ ይህም በንጹህ እጅ እና ልብ ማገልገል ነው።
ማንኛውም ተመራጭ ወደ ፓርላማ ሲገባ ይዞት የሚገባው ትልቁ ስንቅ የሕዝብ አደራ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሰመሩበት፣ ተመራጮች “እጃቸው እና ልባቸው ንጹህ ሆኖ” ሊያገለግሉ ይገባል።
ይህ ማለት ሁሉም የፓርላማ አባላት ከሙስና፣ ከግል ጥቅም፣ ከብልሹ አሠራር እና ከአድልዎ የጸዳ የሥነ-ምግባር ልዕልና ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው። የሕዝብ እንደራሴነት ሥልጣን የሕዝብን አንገብጋቢ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ እንጂ፣ የግል ወይም የቡድን ፍላጎት ማሟያ መሣሪያ መሆን እንደሌለበት በተግባር የማረጋገጥ ኃላፊነት የሁሉም ተመራጮች ነው።

ሁለተኛው የፖለቲካ ብስለት ሲሆን ከ“እኔ ብቻ ላሸንፍ” ትርክት መውጣትን ይጠይቃል። በምርጫ ወቅት የነበረው ፉክክር አብቅቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምልዕክታቸው “እልህ፣ ቁጣ፣ ክርክር፣ አሸንፋለሁ እና እሸነፋለሁ” የሚሉትን የፖለቲካ መንገዶች ማስቀረት እንደሚገባ ማስገንዘባቸው ይታወሳል። ይህ ለሁሉም ተመራጮች ትልቅ ትምህርት ነው።
ፓርላማው የጤናማ የሐሳብ ሙግት የሚካሄድበት፣ ሁሉም ተመራጮች የፓርቲ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው፣ በሀገራዊ ደኅንነት፣ በሰላም እና በልማት ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ለሀገር የሚበጅ መፍትሔ የማመንጨት ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት አውድማ መሆን አለበት። ትልቁ አሸናፊነት ለሀገር የሚበጀውን የጋራ ሐሳብ ማዳበር ነውና።
ሕይወትን የሚቀይር የሥራ ትጋት በማሳየት የሕዝብን ውለታ መክፈል ሌላኛው የተመራጮች ኃላፊነት ነው።
“ደከመን ታከተን ሳይሉ ያመነኝን ሕዝብ እንዴት አገለግላለሁ? ሕይወቱን እንዴት እቀይራለሁ?” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ፣ የየዕለቱ የተመራጮች የሕሊና ሚዛን ሊሆን ይገባል።
ሕዝቡ ድምፅ የሰጠው የኑሮ ጫናው እንዲቀልለት፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ እና ሰላሙ እንዲረጋገጥ ነው። ስለሆነም፣ እያንዳንዱ ተመራጭ ሕግ በማውጣት፣ አስፈጻሚውን አካል በመቆጣጠር እና በመከታተል እንዲሁም ፖሊሲዎችን በመገምገም የሕዝብን የዕለት ተዕለት ሕይወት በተጨባጭ የሚቀይር አሠራር እንዲሰፍን ያለመታከት የመሥራት ግዴታ አለበት።

ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የማድረስ ራዕይ ሰንቆ መሥራትም ከተመራጮች የሚጠበቅ ወሳኝ ኃላፊነት ነው።
በዚህ የታሪክ አጋጣሚ የሕዝብ ውክልና ያገኙ ተመራጮች የተጣለባቸው አደራ የዛሬን ችግር ከማቃለል አልፎ የነገይቱን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የመወሰን ጉዳይ ነው።
ኃላፊነታቸው የዚህን ሀገር ታሪክ የሚቀይሩ መሆን ነው። ይህም ማለት ኢትዮጵያን ከዘመናት የድህነት እና የጦርነት አዙሪት አውጥቶ ወደ ብልጽግና እና ዘላቂ ሰላም ማሻገር የሁሉም ተመራጮች የጋራ ራዕይ እና ግብ መሆን ይኖርበታል።
በአጠቃላይ፣ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተመራጮች የፓርቲ መለያቸው ምንም ይሁን ምን፣ ወደ ፓርላማ ሲገቡ የሚለብሱት አንድ የጋራ ካባ አለ፤ እርሱም የኢትዮጵያ ሕዝብ አገልጋይነት ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር እንደሚያስገነዝበው፣ መራጩ ሕዝብ ግዴታውን ጨርሷል፤ ተረኛው እና ተጠያቂው አካል ተመራጩ ነው።
ስለዚህም ሁሉም ተመራጮች የፓርላማ ጊዜያቸውን እልህና ቁጣን በማስወገድ፣ በንጹህ ልቦና፣ ለሕዝብ ውለታ በመክፈል እና የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሻገር ሊያሳልፉት ይገባል።
በዮናስ በድሉ