በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከ24 ዓመታት በላይ ያገለገለው አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳንኤል ታደሰ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት በቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
ጋዜጠኛ ዳንኤል ታደሰ ከአባቱ ከሻምበል ታደሰ ዳምጠው እና ከእናቱ ከወይዘሮ ፈልቀች ዳኜ ታኅሣሥ 16 ቀን 1959 ዓ.ም ነው በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው።
ለቤተሰቡ 7ኛ ልጅ የሆነው ዳንኤል፣ ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አብነት አካባቢ በሚገኘው ብርሃነ ህይወትና አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሽመልስ ሀብቴ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡
የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በ1985 ዓ.ም ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ትምህርቱን ተከታትሎ ተመርቋል፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳንኤል ታደሰ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለበርካታ ዓመታት ከሪፖርተርነት እስከ ከከፍተኛ አዘጋጅነት በሙያው አገልግሏል።
በኢትዮጵያ ሬዲዮ የቅዳሜ መዝናኛ፣ የሬዲዮ እንግዳና የአፍሪካ ሙዚቃ በተሰኙ ፕሮግራም አዘጋጅነት የሰራ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አርሂቡ ፕሮግራም፣ የበዓል የመድረክ ዝግጅቶችን በተለያዩ ክልሎች ተጉዞ በመስራት በአድማጮች ዘንድ ተወዳጅ ጋዜጠኛ ሆኖ አልፏል።
ጋዜጠኛ ዳንኤል ለሥነ-ጽሑፍ ከነበረው ፍቅር የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት በሚታተሙ የግል መጽሔቶች እና ጋዜጦች ግጥሞች፣ አጫጭር ልቦለዶች እና የትርጉም ስራዎች ላይ ዐሻራዎቹን አኑረዋል።
በወጣትነቱ ለሥነ-ጽሑፍ እና ጋዜጠኝነት ባለው ክብር በልዩ የድምፅ ቅላጼው፣ በማራኪ አቀራረቡ እና በሳል የጋዜጠኝነት ብቃቱ በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የተቀረጸ ደማቅ ታሪክ ያለው ጋዜጠኛ እንደነበርም ወዳጅ ጓደኞቹ ይመሰክራሉ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም ለአድናቂዎቹ እና የስራ ባልደረቦቹ መፅናናትን ይመኛል።
በሔለን ተስፋዬ