ኢትዮጵያ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያስመዘገበችው ስኬት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዋን ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋገረ ታሪካዊ ክንውን ሆኗል።
ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ እስከ ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ድረስ የታየው ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ኢትዮጵያ በሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር መንገድ ላይ መጽናቷን በይፋ አሳይቷል።
ከ94 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመዘገበ መራጭ ሕዝብ በምርጫው መሳተፉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ሥልጡን እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሸጋገሩን የሚያረጋግጥ ነው።
በምርጫ ሂደቱ የተንጸባረቀው የሕዝብ ንቃት ለውጥን በድምፅ የመወሰን ባህል በኢትዮጵያ ውስጥ ሥር እየሰደደ መምጣቱን ያሳያል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ምርጫውን በቴክኖሎጂ የታገዘ እና ለዜጎች ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ማከናወኑ፣ የተቋሙ አቅም መገንባቱን በግልጽ ያሳየበት ክንውን ሆኗል።
ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን ተከትሎ አሁን ትኩረቱ ወደ መንግሥት ምሥረታ ሂደት ተቀይሯል።
በተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ቁጥር አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የተከተለ መንግሥት ይመሠረታል።
የተመረጡት አካላት ሕዝቡ የሰጣቸውን አደራ በመቀበል የኢትዮጵያን የልማት እና የብልጽግና ጉዞ በሚቀጥሉት ዓመታት በብቃት እንዲመሩ ይጠበቃል።
ለሀገራችን የፖለቲካ መረጋጋትን ያመጣው ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ በዲጂታል ሽግግር፣ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌሎች ስትራቴጂካዊ የልማት ሥራዎች የጀመረችውን እንቅስቃሴ ይበልጥ ያፋጥነዋል።
ከምርጫ እስከ መንግሥት ምሥረታ ያለው ይህ ሂደት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጸብ እና ከአምባጓሮ ተላቅቆ በዕውቀት እና በፖሊሲ አማራጮች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለዓለም ያሳየ ነው።
በሃና ምንዳሁን