Search

ኢትዮጵያ ነገዋን ለመገንባት ማንሰራራት ጀምራለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ሰኔ 16, 2018 47

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ኢትዮጵያ ነገዋን ለመገንባት ማንሰራራት መጀመሯን "ኢትዮጵያ ታከናውናለች" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው መድረክ ላይ አብስረዋል፡፡

ሀገራት ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ ወደፊት ለመራመድ ድፍረትን ወደሚጠይቅ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንደሚደርሱ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት ይህን መሰል ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ መሆኗን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የኢትዮጵያ የአሁኑ ጉዞ የሌሎችን ፈለግ መከተል ወይም እኩል ለመድረስ መሞከር ሳይሆን መመንጠቅ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህን መሰሉን ወሳኝ ጊዜ ሀገራችን እንደምትረዳው እና ከዚህ ቀደምም አሳልፈነው እንደምናውቅ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መኖሪያ የሆነች፣ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የኖረች ጥንታዊት ሥልጣኔ ባለቤት፣ እንዲሁም በተደጋጋሚ የሚሰጡ ዝቅተኛ ግምቶችን ሰብራ ከፍ ማለት የቻለች ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።

ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሕዝቧ ጥረት መገንባት የቻለች ሀገር መሆኗንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ ሀገራችን ፈጣን ዕድገት ለማምጣት ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪው ትውልድ ጠንካራ አቅም እና መሰረት ለመገንባት የሚያስችሉ ሪፎርሞችን በማካሄድ ላይ እንደምትገኝ አብራርተዋል።

የዚህ ሥራም ማዕከል የራሳቸውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እየገነቡ እና በክብር አስተዋጽዖ እያበረከቱ ያሉ ዜጎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ ባላት አቅም እና ጸጋ ሳይሆን በችግሮቿ ስትገለጽ መቆየቷን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ሆኖም ዛሬ በኢኮኖሚያችን፣ በተቋማቶቻችን እና በማኅበረሰቦቻችን ውስጥ የተለየ ታሪክ እየተጻፈ እና እውን እየሆነ ነው" በማለት ስኬታማ ጉዞዋን አብስረዋል።

ይህ ጉዞ የሌሎችን ፈለግ ከመከተል ባለፈ የሀገራችንን ብሩህ ተስፋ እና የእውነተኛ ማንሰራራት መንገድ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የከባድ ውሳኔዎች እና የዘላቂ ጥረቶች ውጤትን ማየት መጀመራችንን አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

በለሚ ታደሰ