ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደች ያለችውን ሁሉን አቀፍና መዋቅራዊ ለውጥ በግልጽነት እያሳየች መሆኑንና በጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ አጋርነትን አጥብቃ እንደምትሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታዉቀዋል።
በአሁኑ ወቅት መላው ዓለም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ለውጥ በአድናቆት፣ እየተከታተለው መሆኑን ጠቁመዉ የመንግሥት ዋነኛ እና የማይናወጥ ግዴታ የሕዝቧን ዘላቂ ፍላጎትና ምኞት ማገልገል መሆኑን ተናግረዋል።
የለውጥ ሥራዎች ቀዳሚ ግብ የዜጎችን ዕድሎች ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ ማስፋት እንዲሁም ጠንካራ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂነት ያላቸውን ተቋማት መገንባት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የሚገነቡት ተቋማት እና መሠረተ ልማቶች ክልሎችን፣ ማኅበረሰቦችን እና ትውልዶችን በጋራ ብልጽግና ማገናኘት የሚያስችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም ትውልድ የሀገር ግንባታ ሥራን ፈጽሞ ብቻውን አጠናቅቆ እንደማያበቃ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም እያንዳንዱ ትውልድ ካለፈው የተረከበውን ዋጋ ያለው እሴት የመጠበቅ እና የማስተካከል እንዲሁም ቀጣዮች የሚገነቡበትን መሠረት የማጠናከር የታሪክ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው የለውጥ እና የማሻሻያ ሥራዎችም ይሄንኑ ታሪካዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እና ወደፊት ለመጓዝ የምታደርገው ጥረት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በበረከት ሽመልስ