Search

መስከረም ላይ የሚመረቀው የሕዳሴ ግድብ ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት የጀርባ አጥንት ነው - ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

ሓሙስ ነሐሴ 08, 2017 116

ኢትዮጵያ በመስከረም ወር የምታስመርቀዉ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት የጀርባ አጥንት መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የውኃ ኢንቨስትመንት ሰሚት (AU AIP Africa Water Investment Summit 2025) ጉባዔ  የሁለተኛ ቀን ውሎ በሚንስትሮች ከፍተኛ የፓናል ውይይት ላይ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተጠይቀው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ቀደም ባሉት መንግስታት ዘመን እንዲጀመር ታስቦ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን የበጀት ድጋፍና ብድር ቢጠየቅም ማግኘት አለመቻሉን አስታውሰዋል። በዚህም የተነሳ የዛሬውን ትውልድ ሃላፊነቱን እንዲወስድ ተገድዷል ብለዋል፡፡

ግድቡ በዋናነት በመንግስት አቅም እና በሀገር ውስጥ እና ባህር ማዶ በሚገኙ ውድ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት ቀጥታ ተሳትፎ የተገነባ የአፍሪካ ኩራትና የኃይል ምንጭ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ሚኒስትሩ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በዋናነት በግሉ ዘርፍ ላለው ክፍለ ኢኮኖሚ በእጅጉ ትልቅ የኢንቨስትመንት ዕድል ይዞ ይመጣል ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም ግድቡ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ከ5,150 ሜጋ ዋት (5.15ጊጋ ዋት) የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው አስታውሰው፤ የግድቡ ግንባታ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች በቀጥታ በመሳተፍ አሻራቸውን ያስቀመጡበት እና ከኃይል ምንጭነት በዘለለ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ዋና ምሰሦ ነው ብለዋል፡፡

በዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ የውኃና ኃይል አቅርቦት የጀርባ አጥንት ሆነው ለሌሎች ግቦች በአማካኝነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ሚንስትሩ በማሳያነት አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትሥሥርን በመፍጠር ረገድ በቀዳሚነት ሚናዋን እየተጫወተች መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ከሱዳን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ታንዛኒያ እና ሌሎች ሀገራት ጋር የኃይል አቅርቦት እያመቻቸች እንደምትገኝ እና ከሌሎች ቀሪ ሀገራት ጋር ስምምነቶች ተደርገው በሂደት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ሚንስትሩ ኢትዮጵያ በማጠናቀቅ ላይ ስላለችው ታላቁ የአትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ፕሮጀክቱ ፋይናንስ ስለተደረገበት ሁኔታ ተሞክሮዋን እንድታካፍል በጉባዔው ላይ ተጠይቀዋል፡፡

ሚንስትሩ በጉባዔው የሰጡትን ማብራራያ ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት የውኃ ሚንስትሮች እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ከሚንስትሩ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።

በተለይም የዚምባቡዌ የውኃ እና ግብርና ሚንስትሩ በቀጥታ የተሞክሮ ልምድ ለመቅሰም ከጠየቁ መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።