በክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና ውጤት የሴት ተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ መሻሻልን አሳይቷል ሲል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በሰጡት መግለጫ፤ የክልል አቀፍ 8ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱት 36 ሺ 683 ተማሪዎች መካከል 20 ሺ 744 ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ ማለፋቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ ውስጥ 9 ሺ 731 ተማሪዎች ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት አቶ አልማው የሴት ተማሪዎች የማለፍ ምጣኔው በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና የሴቶች ውጤት ከወንዶቹ የተሻለ ሆነ መገኘቱንም አስታውቀዋል።
አጠቃላይ የማለፍ ምጣኔው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለፁት አቶ አልማው ከዘንድሮ ውጤት በመነሳት በቀጣይ በትምህርት ጥራት ላይ የሚሰሩ በርካታ ተግባራት እንዳሉም አስረድተዋል።
በክልሉ የ8ኛ ክፍል አጠቃላይ ተፈታኞች የማለፍ ምጣኔ ከአለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ተናግረዋል።
የፈተና አስተዳደር ስርዓት ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ተማሪዎች በራስ አቅም ብቻ ታግዘው እንዲመዘኑ ከማስቻሉም በላይ ሁሉም ባለድርሻዎች በትምህርት ጥራት ላይ እንዲያተኩሩ አስችሏል ብለዋል።
በመጪው የትምህርት ዘመን በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ትምህርት ቤቶችን ምቹ የመማሪያ ስፍራ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ከ 120 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሕጻናት ተማሪዎችን በእራስ አገዝ አቅም ለመመገብ የሚያስችል ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ግብዓቶችን ተደራሽ ለማድረግ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተጠቁመዋል።
ከ 1.2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የመማሪያ እና ማስተማሪያ መሐፍት የዘመኑ ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ ለትምህርት ቤቶች የማሰራጨት ሥራ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶችን ቀጣይ ለማድረግ ቢሮው ባለድርሻዎችን አቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በሰለሞን ባረና
#EBC #ebcdotstream #climatechange