የዲያስፖራውን ማህበረሰብ በሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ አጀንዳቸውን በመስጠት በአካል ተሳትፎ እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ ዝግጅቱን አጠናቆ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ አከናውኗል።
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም እ.ኤ.አ ከነሀሴ 30/2025 ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ በሚዘጋጀው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ዝግጅቱን እንደጨረሰ የኮሚሽኑ የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ዲያስፖራው ማሕበረሰብ አስተባባሪ ረታ ጌራ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ተሳታፊዎችን የሚያስመርጥ መርሐ-ግብር እንደሚያከናውንም አስተባባሪው ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
ዲያስፖራው ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸውን አጀንዳዎች ይዞ በመገኘት፤ በሂደቱ ላይ እንዲሳተፍም ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀርባል ነው ያሉት።
በምክክሩ ሂደት ኮሚሽኑ ለዳያስፖራው ማሕበረሰብ እስካሁን የሰራቸውን ሥራዎች የሚያቀርብበት ሁኔታ እንደሚኖርም አንስተዋል።
የኮሚሽኑ የምክክር ሂደት በቀጣይም በሰሜን አሜርካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ በካናዳ ቶሮንቶ ፣በዩናይትድ ኪንደም ለንደን፣ በስዊዲን ስቶኮልም እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ዱባይ ይካሄዳልም ብለዋል።
መሳተፍ የማይችሉት በዙም ቴክኖሎጂ መሳተፍ የሚችሉበትን አግባብ ኮሚሽኑ ማመቻቸቱንም አስተባባሪው ረታ ጌራ ተናግረዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ