የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ በትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የራሱን አሻራ ማሳረፉን፤ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ለዚህም አንዱ ማሳያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሆኑን አንስተው፤ ዛሬ ፍጻሜው ለተቃረበው ግድብ የተጓጓዙ መሣሪያዎች በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እንዳለፉም ተናግረዋል።
ይህ የተባለው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዓመታዊ አፈፃፀም ጉባዔ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር )፤ የሎጂስቲክስ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማገዝ ውጤታማ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ በመድረኩ ላይ ገልጸዋል።
ዘርፉ ቅንጅታዊ አሠራሩን በማጎልበት ለሀገር ፈጣን የኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ እንዲቀጥል ትኩረት እንደሚሰጠውም ነው ያነሱት።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፥ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የመንገድ ደህንነት እና የዜጎችን ሕይወት ለመጠበቅ እንዲሁም ውድመትን ለመታደግ ትርጉም ያላቸው ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
በነስረዲን ሀሚድ