ታዋቂው አፍሪካን ፈርስት ፖስት እንደዘገበው፣ ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ አቅሟን ለማሳደግ በኒውክሌር ኃይል እና ቴክኖሎጂ ልማት መስክ ከዓለም አቀፍ ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር በስፋት እያጠናከረች ትገኛለች።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በዘርፉ አቅሟን ለመገንባት ከአሜሪካ እና ከሩሲያ ጋር የሚደረጉ የትብብር እንቅስቃሴዎችን በፍጥነት እያሳደገች ነው።
የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ለኢንዱስትሪ፣ ለህክምና፣ ለግብርና እና ለንጹህ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይታመናል።
የሩሲያው አቶሚክ ኤጀንሲ (Rosatom) እና የአሜሪካ የቴክኖሎጂ አካላትም በዘርፉ የቴክኒክ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የደኅንነት ድጋፎችን ለመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው በዘገባው ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤጀንሲ (IAEA) መመሪያዎች እና ደንቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ የኒውክሌር መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ ይህ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ተጨማሪ ትልቅ አቅም ይፈጥርላታል።
በሂደቱም ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለሰው ኃይል ስልጠና ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ባለሙያዎቹ አክለው ጠቁመዋል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: