የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የ5ኛውን ዙር ብሔራዊ የ“ሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ቻሌንጅ” ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ማካሄድ ጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የተውጣጡና ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ክህሎት ያላቸው ከ1 ሺህ በላይ ሰልጣኝ ወጣቶች እየተሳተፉ ሲሆን፣ የክረምት እረፍት ጊዜያቸውን በፈጠራና በክህሎት ማደራጃ መርሐ ግብሮች የሚያሳልፉ ይሆናል።
በካምፑ ከሳይበር ደኅንነት እና ቴክኖሎጂ ስልጠናዎች ጎን ለጎን የሰልጣኞችን አጠቃላይ ጤንነት እና ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬ የሚያጎለብቱ ስልጠናዎችና የቼዝ ጨዋታን ጨምሮ ሌሎች የፈጠራ እና የማሰላሰል ክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ሰልጣኞች የቋንቋ፣ የባህል እና የተለያዩ ማኅበራዊ ልምዶችን የሚያካፍሉበትና የሚያዳብሩበት መድረክ እንዲሁም ወጣቶች በሥነ-ምግባር የታነጹ፣ በቴክኖሎጂ የዳበሩ እና ለሀገር አጋዥ እንዲሆኑ የሚያስችል ስልጠና እንደሆነም ተመላክቷል።
የዘንድሮው የሳይበር ታለንት የክረምት ካምፕ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይወሰን፣ በሀገራችን በተመረጡ 6 ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት እየተካሄደ ይገኛል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከዚህ ቀደም በዚሁ ዘርፍ የበርካታ ወጣቶችን ልምድ እና ክህሎት ለማዳበር የሚያስችሉ ተመሳሳይ የካምፕ ፕሮግራሞችን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል።
በመሓሪ ዓለሙ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: